የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አርማ

1 ጥር 2024, 17:58 EAT

በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ ኦፕሬሽን ከ5 ሺህ 536 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።

የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ታኅሣሥ 22፣ 2016 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከታኅሣስ 6 እስከ 11፣ 2016 ዓ. ም. ድረስ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ኦፕሬሽን እንደተካሄደና ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም ተጠቁሟል።

ፋና መግለጫውን አጣቅሶ እንደዘገበው፣ በዚህ ኦፕሬሽን ወቅት “ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ከበርካታ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸው” ተገልጿል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋን ጠቅሶ ፋና እንደዘገበው፣ “ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የሚያውኩ የዝርፊያ፣ ቅሚያ እና ተያያዥ ወንጀሎችን” በተመለከተ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ረዳት ኮሚሽነሩ የቅሚያ ወንጀል በተሽከርካሪና በአካል የሚካሄድባቸው እንዲሁም ወንጀል የሚጠነሰስባቸው ስፍራዎች እና ቤቶች ላይ “በተባባረ ክንድ እየተሠራ መሆኑን” መግለጻቸውም ተዘግቧል።

በዚህ ኦፕሬሽን 1 ሺህ 114 የቁማር ቤቶች፤ 176 ሺሻ ቤቶች እንደታሸጉ እንዲሁም፣ በመኖሪያ ቤቶች 73 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ እንደተያዘም ተገልጿል።

በተጨማሪም “ሕፃናትን በመሰብሰብ የተለያዩ አልባሌ ተግባራትን የሚያስፋፉ እና ትውልድ የሚያጠፉ” የተባሉ 164 ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውም ተገልጿል።