
ከ 9 ሰአት በፊት
ቪላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ጥቃቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ። ፑቲን ይህን ያሉት አገራቸው ሩስያ በዩክሬን ላይ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት እየሰነዘሩ ባለችበት ወቅት ነው።
ፑቲን በሞስኮ የሚገኝ ወታደራዊ ሆስፒታል ከጎበኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ ቁልፍ የዩክሬን መሠረተ ልማቶች ዒላማ ተደርገው ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል ሲሉ ዝተዋል።
ዩክሬን በሩሲያ የቤልጎሮድ ከተማ ላይ የሰነዘረችውን የአየር ጥቃት ፑቲን ‘ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የተቃጣ ሽብር’ ሲሉ ጠርተውታል።
በቅዳሜው የዩክሬን የአየር ጥቃት 25 ሰዎች መገደላቸውን ዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
ፑቲን ለወታደሮቻቸው ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ደግሞ በጦርነቱ አገራቸው የበላይነት እየያዘች መሆኑን ካወሱ በኋላ ይህ ጦርነት ቶሎ እንዲጠናቀቅ እንደሚሹ ገልጠዋል። ይሁንና ጦርነቱ ማለቅ ያለበት የሩሲያን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ብቻ እንደሆነ አስምረውበታል።
ፑቲን ይህን ጦርነት እንዳያበቃ ዋና እንቅፋት የሆኑት ምዕራባዊያን ናቸው ብለዋል። ይሁንና አሁን አሁን ምዕራባዊያን ሩስያ ሸብረክ እንደማትል እየገባቸው ስለመጣ መለሳለስ ጀምረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ባላንጣቸው ዘለነስኪ በበኩላቸው ለኢኮኖሚስት መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ ‘ሩስያ ጦርነቱን እያሸነፈች ነው’ የሚለው ወሬ መሬት ላይ የማይታይ ‘ተምኔታዊ’ ሲሉ ገልጸውታል።
ዘለንስኪ ይህን ሲያብራሩ ሩስያ በጦርነቱ ምን ያህል ወታደሮችን እንዳጣቸው በማስታወስ ነው።
ሩስያ በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት አንድም የዩክሬን ከተማ መቆጣጠር እንዳልቻለች ያወሱት ዘለንስኪ ሞስኮ ጦርነቱን እያሸነፈች ነው የሚባለው ምኑ ላይ ነው ሲሉ ጠይቀዋል።
- ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራረመች1 ጥር 2024
- በአዲስ አበባ ከ5 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ1 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ የአየር መንገዱን ድርሻ ሰጥታ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ በሊዝ ልትወስድ መሆኑ ተገለጸ2 ጥር 2024
ዘለንስኪ ከኢኮኖሚስት ጋር በነበራቸው ቆይታ አጋሮቻቸውን ጭምር ኂሰዋል። የምዕራብ አጋሮቻችን የኛ ጥድፊያ አይገባቸውም፤ እኛን ለማገዝ ጊዜ ይወስዳሉ ብለዋል።
ፑቲንና ዘለንስኪ አዲሱን የፈረንጆች ዓመት አስመልክተው ለሕዝቦቻቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
ፑቲን በመልእክታቸው ወታደሮቻቸውን ”ጀግኖች” ሲሉ አወድሰዋል።
ዘለነስኪ በበኩላቸው አገራቸው የምታመርታቸው የጦር መሣሪያዎች በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ ካወሱ በኋላ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ድሮን እንሠራለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የሩስያና ዩክሬን ከተሞች ባለፉት ጥቂት ቀናት ከባድ ጥቃቶችን ሲያስተናግዱ ነበር።
ዩክሬን በሩስያ ቁጥጥር ሥር ያለውን ዶኔስክ ግዛት በአዲስ ዓመት ዋዜማ በአየር ደብድባለች። በጥቃቱ አራት ሰላማዊ ሰዎች ሞተውብኛል፤ 13 ቆስለውብኛል ብላለች፣ ሩስያ።
ቅዳሜ ዕለት ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሩስያ ቤልጎሮድ ከተማ ዩክሬን በሰነዘረችው ጥቃት በርካቶች ተገድለዋል። ፑቲን ይህን ጥቃት ‘ሽብርተኝነት’ ሲሉ ጠርተውታል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሩስያ በዩክሬን በርካታ ከተሞች ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን ስትሰነዝር ነበር። በነዚህ ጥቃቶች በድምሩ 45 ሰዎች ተገድለዋል።
እነዚህ ተከታታይ ጥቃቶች ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከባድ የሚባሉ የሚሳኤል ጥቃቶች ናቸው ሲሉ የዩክሬን ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።