የኖቤል ተሸላሚው ፕ/ር ሙሐማድ ዩኑስ

ከ 9 ሰአት በፊት

የባንግላዲሽ ፍርድ ቤት የኖቤል ተሸላሚው ፕ/ር ሙሐማድ ዩኑስ ለስድስት ወራት እንዲታሰሩ አዘዘ።

ፍርዱ የተላለፈው ፕ/ር ሙሐማድ የአገሪቱን የሠራተኛ ሕግ ተላልፈዋል በሚል ነው።

ታዋቂው የምጣኔ ሀብት ባለሙያና እሳቸው በመሠረቱት ግራምን ቴሌኮም ተቋም የሚሠሩ ሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸው ለተቋሙ ሠራተኞች ልዩ የክፍያ ሥርዓት በማዘጋጀት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ሠራተኞቹ የተለያየ እክል ሲገጥማቸው የሚገለገሉበት ገንዘብ የሚሰጥበት ሥርዓት (ዌልፌር ፈንድ) ነበር ያቋቋሙት።

አራቱም ተከሳሾች ስህተት አልሠራንም ሲሉ ተከራክረዋል። በጊዜያዊነት በዋስ እንዲወጡ ፈቃድ ተሰጥቷል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ፕ/ር ሙሐማድ “ጠበቆቼ በአሳማኝ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መከራከሪያ መሠረት ፍርዱ ከምክንያታዊነት የራቀ ነው” ብለዋል።

“የባንግላዲሽ ሕዝብ ኢ-ፍትሐዊነትን በአንድ ድምጽ እንዲያወግዝና ለሁሉም ዜጎች ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት እንዲቆም እጠይቃለሁ” ሲሉም አክለዋል።

የ83 ዓመቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በመላው ዓለም የሚታወቁት ‘የድሆች መጠለያ’ በሚል ስም ነው።

በማይክሮ ፋይናንስ ቀዳሚ ሥርዓት በመገንባትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት በማውጣት ይታወቃሉ።

ፕሮፌሰሩ እንዲሁም የመሠረቱት ግራመን ባንክ እአአ በ2006 ኖቤል ተሸልመዋል።

ከጠበቆቻቸው አንዱ አብዱላህ አል ማሙን “ያልተጠበቀ ውሳኔ ነው። ሕግን ያልተከተለና የተጣደፈ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ሐሳቡ ዓለም አቀፍ ምሥላቸውን ማጠልሸት ነው። ይግባኝ እንላለን” ሲሉም አክለዋል።

ከሠራተኞች ሕግ ጋር ይጻረራሉ በሚል ሌሎች 100 ክሶችም አሉባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሲና ሼክ የፕሮፌሰሩን ባንክ በአንድ ወቅት ‘ደም መጣጭ’ ሲሉ ገልጸውታል። ወለድ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመርም ከሰዋል።

የቀድሞ የአምነስቲ የመብቶች ክፍል ኃላፊና አሁን በልዩ ልዑክነት በተባበሩት መንግሥታት የሚሠሩት አይሪን ካን፣ ለኤኤፒ እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “የፍትሕ መዛባት” ነው።

ባለፈው ነሐሴ 170 ዓለም አቀፍ የታዋቂ ሰዎች ስብስብ የባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮፌሰሩን ‘ማንገላታት’ እንዲያቆሙ ጠይቀው ደብዳቤ አስገብተዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፣ የቨርጅን ግሩፕ መሥራች ሪቻርድ ብራንሰን፣ የዩቱ መሪ ድምጻዊ ቦኖና ሌሎችም ፈርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ግን ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የፍርድ ሂደቱን እንዲከታተሉ ጋብዘዋል።

ፕ/ር ሙሐማድ፤ አዋሚ ሊግ ፓርቲን የሚቀናቀን የፖለቲካ ፓርቲ ሊያቋቁሙ ስለሚችሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ጋር መሻከር ተፈጥሯል የሚሉ ቢኖሩም በትክክል የተከሰተው ግልጽ አይደለም።