ሊ ጃይ-ማዩንግ

ከ 9 ሰአት በፊት

የደቡብ ኮሪያው ተቃዋሚ መሪ በአገሪቱ ደቡባዊ የወደብ ከተማ ቡሳን ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት በስለት መወጋታቸውን ዮንሃፕ የተባለው የዜና ወኪል ዘግቧል።

እአአ በ2022 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጠባብ ውጤት የተሸነፉት ሊ ጃይ-ማዩንግ ማክሰኞ ጠዋት አንገታቸው ላይ ተወግተዋል ተብሏል።

ጥቃት አድራሹ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሏል።

አንድ ሴንቲሜትር ያህል ጉዳት የደረሰባቸው ሊ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ተከታትለዋል። ቁስሉ ለሕይወታቸው አስጊ አይደለም ሲል ፖሊስ ገልጿል።

በ50ዎቹ ወይንም በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ ወደ ሊ የቀረበው አድናቂያቸው በመምሰል ፊርማቸውን በመጠየቅ መሆኑ ተገልጿል።

ጥቃቱ ሲደርስ የሚያሳዩት እና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉት ቪዲዮዎች ሊ ከጥቃቱ በኋላ መሬት ላይ ሲወድቁ ያሳያሉ።

ብዙ ሰዎች አጥቂውን ተጨማሪ ጥቃት እንዳያደርስ ለመግታት ሲሞክሩ ታይተዋል። ከክስተቱ በኋላ የተነሱ ፎቶግራፎች ላይ ሊ መሬት ላይ ዓይናቸውን ጨፍነው ተኝተው ሲያሳይ አንድ ግለሰብ ደግሞ በመሀረብ ቁስላቸውን ሲሸፍን አሳይተዋል።

በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱም ዮንሃፕ ጨምሮ ዘግቧል።

የ59 ዓመቱ ሊ የኮሪያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የደቡብ ኮሪያ ህግ አውጪ አባል ባይሆኑም ከወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል።

እአአ በ 2022 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በ0.73 በመቶ የድምጽ ልዩነት በአሁኑ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል ተሸንፈዋል። ይህ ምርጫ በደቡብ ኮሪያ ታሪክ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ፕሬዝዳንታዊ ውድድር አድርጎታል።

እአአ በ 2027 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩም በሰፊው ይጠበቃል።

ከምርጫው ወዲህ ከሴኡል በስተደቡብ በምትገኘው እና አንድ ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት የሴኦንግናም ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት የግል አልሚዎች ከንብረት ፕሮጀክት በህገ ወጥ መንገድ እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል በማለት አቃብያነ ህጎች በሙስና እና በእምነት ማጉደል ክስ መስርተውባቸዋል። ሊ ክሶቹን ውድቅ ከማድረግ ባለፈ ፖለቲካዊ ነው ብለውታል።

ፍርድ ቤት በመስከረም ወር በተከሰሱበት ጉዳይ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የቀረበለትን የአቃቤ ህግ ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። አቃቤ ህግ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከሙስና ጋር በተያያዙ ሌሎች በርካታ ክሶች እየመረመራቸው ነው።

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የፕሬዝዳንት ዮንን የውጭ እና የሀገር ውስጥ ፖሊሲዎችን በመቃወም የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ነው። በአድማው ምክንያት ሊ ሆስፒታል ገብተው ለመታከም ተገደዋል።

የደቡብ ኮሪያ ፖለቲከኞች በጦር መሳሪያ አካላዊ ጥቃት ሲደርስባቸው አሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ 2022 ከ ሊ በፊት ፓርቲውን ሲመሩ የነበሩት ሶንግ ያንግ-ጊል ለ ሊ ምርጫ ዘመቻው ሲያከናውኑ በደረሰባቸው ጥቃት ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።

እአአ በ 2006 ደግሞ የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ የሆኑት እና በኋላ ላይ ፕሬዝዳንት ለመሆን የቻሉት ፓርክ ጊዩን-ሃይ በደረሰባቸው የስለት ጥቃት አሁንም ድረስ የሚታይ ጠባሳ ፊታቸው ላይ ጥሎባቸው አልፏል።