የሱማሌላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሱማሌላንድና ኢትዮጵያ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ የአገርነት እውቅና ለመሰጠት መስማማቷን አረጋግጧል። ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ የአገርነት እውቅና ለማግኘት ለረጅም ጊዜ ስትጥር መቆየቷን መግለጣቸውን ሚንስቴሩ ጠቅሷል። በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት፣ ሱማሌላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር በር በ50 ዓመት የሊዝ ኪራይ ለመስጠት መስማማቷንም ሚንስቴሩ ገልጧል። ስምምነቱ፣ በኹለቱ አገሮች መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያረጋግጥም ሚንስቴሩ የጠቀሰ ሲኾን፣ ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የባለቤትነት ድርሻ እንድታገኝ እንደሚያስችላት ፕሬዝዳንት ቢሂ ትናንት የጠቀሱትን ነጥብ ግን አላነሳም። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ ምስጋኑ አረጋ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱማሌላንድን መግለጫ እንደሚቀበለው በ”ኤክስ” ገጻቸው አረጋግጠዋል።
ሱማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ራስ ገዝ ጋር የደረሰችበት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት “ሉዓላዊነቴን የጣሰ” እና “ዋጋ ቢስ” የኾነ ስምምነት ነው በማለት አውግዘዋለች። ሱማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ባስቸኳይ የጠራች ሲኾን፣ አምባሳደር አብዱላሂ ዋርፋ ዛሬውኑ ወደ ሞቃዲሾ መሄዳቸው ታውቋል። አምባሳደሩ ለውይይት ባስቸኳይ እንዲጠሩ ውሳኔ ያሳለፈው፣ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የባሕር በር ስምምነት ዙሪያ ዛሬ ጧት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የመከረው የአገሪቱ ካቢኔ ነው። የካቢኔውን ልዩ ስብሰባ የመሩት የሱማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ባሬ፣ መንግሥታቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጠዋል። ባሬ፣ የትኛውም አካል የሱማሊያን የየብስ፣ የባሕርና የአየር ሉዓላዊ የግዛት ወሰን መጣስ አይችልም በማለት አስጠንቅቀዋል።
የሱማሊያ ፓርላማ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የባሕር በር ስምምነት ላይ ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ መክሯል። ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር፣ የሱማሊያ የግዛት አንድነት ለድርድር የማይቀርብና የማይሸራረፍ ነው በማለት ተናግረዋል። ሱማሊያ አኹን ከድሮው በተሻለ ኹኔታ ውስጥ መኾኗን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ የኢትዮጵያ ድርጊት አልሸባብ እንደገና እንዲያንሠራራ ሊያደርግ የሚችል ነው ማለታቸው ተሰምቷል። ሱማሊያ፣ የኢትዮጵያ ድርጊት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ አደጋ የሚደቅን መኾኑን በመግለጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና አፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲቀመጡ ጠይቃለች። አልሸባብም፣ ስምምነቱን አውግዞ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም መዛቱን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።