
ከ 4 ሰአት በፊት
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ “የዘር ማጥፋት” ድርጊቶችን እየፈጸመች ነው ማለቷን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ልትሞግት ነው ሲሉ የእስራኤል ቃል አቀባይ ገለፁ።
“ታሪክ ይፈርድባችኋል፤ ያለ ምሕረትም ይፈርድባችኋል” ሲል ኢሎን ሌቪ ለደቡብ አፍሪካ መሪዎች ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረቧ እስራኤልን አስቆጥቷል።
ደቡብ አፍሪካ የፍልስጤማውያን የነጻነት ትግል ደጋፊ ስትሆን መስከረም 26 በጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስራኤልን ደጋግማ አውግዛለች።
በእስላማዊው ቡድን ሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ22 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል ።
ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ ከፍተኛ ጥቃት በማድረስ ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና 240 ያህሉን አግቶ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በሐማስ ላይ ጦርነት አወጃለች።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ለአይሲጄ ባቀረቡት ማመልከቻ አገሪቱ “የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይከሰት የመከላከል” ግዴታ እንዳለባት ገልጿል።
ባለ 84 ገጹ ሰነድ እንደሚያስረዳው “እስራኤል የፈፀመችው ድርጊት እና ግድፈቶች በባህሪያቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል የመፈጸም ሲሆኑ የፍልስጤምን ዘር ለማጥፋት ያለመ ነው” ይላል።
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጠበቆች ጉዳዩ በጥር 11 እና 12 እንዲታይ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ክሌይሰን ሞንዬላ በኤክስ ገጽ ላይ ጽፈዋል።
- የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም አለ2 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አመለከቱ2 ጥር 2024
- ሶማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠራች2 ጥር 2024
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ሄግ ያደረገው አይሲጄ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፍርድ ቤት ነው። በአገራት መካከል አለመግባባቶችን ከመፍታት ባለፈ በዓለም አቀፍ የሕግ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ይሰጣል። የሚሰጣቸው አስተያየቶች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የሕግ አካላት ከፍተኛ ተሰሚነት አላቸው።
እስራኤል ጉዳዩን ለመዋጋት አስባለች ያሉት ኤይ ሌቪሎን “የደቡብ አፍሪካን የማይረባ ”የደም መብጣት” ክስ ትከላከላለች” ብለዋል።
”የደም መብጣት” በእንግሊዝኛው Blood libel የሚባል ሲሆን በተለይም በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ የተጀመረ ስም ማጥፋትን የሚመከለት ነው። ”የደም መብጣት” አይሁድ ማኅበረሰብ የሌሎችም በተለይም የክርስቲያን ሕጻናት ደም ለሃይማኖታዊ ምክንያት ሲባል የማፍሰስ ተግባር ይፈጽማሉ በሚል የሚቀርብባቸው ሐሰተኛ ክስ ነው።
ቃሉ በዋናነት በአይሁድ ማኅበረሰቦች ላይ ፀረ-ሴማዊ የሐሰት ክሶችን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ደቡብ አፍሪካ ክስ መመስረቷን “ተሳስተሻል ደቡብ አፍሪካ! እኛ አይደለንም የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች። እኛ አይደለንም ሃማስ ነው” ሲሉ በንዴት ምላሽ ሰጥተዋል።
“ሐማስ ቢችል ሁላችንንም ይገድለናል:: የእስራኤል ጦር በተቻለው መጠን በሥነ ምግባር እየተመራ ነው::” ብለዋል።
ናታንያሁ ይህን ያሉት እስራኤል “በረዥም ጊዜ ወረራ፣ ሰፈራ እና … የፍልስጤም ግዛት ላይ ጥቃት በመፈጸም” በሚል በፍልስጤማውያን አነሳሽነት በአይሲጄ ምርመራ እየተደረገባት ባለበት ወቅት ነው።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም እአአ በ 2004 በእስራኤል ጉዳይ ላይ አንድ ጊዜ ብይን ሰጥቷል። በዚህም አገሪቱ በዌስት ባንክ እና በሌሎች አካባቢዎች እስራኤል የገነባችው አጥር ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን መሆኑን አረጋግጧል።
አጥሩ የተገነባው ከዌስት ባንክ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃትን ለመከላከል ነው ስትል እስራኤል ገልጻለች። ፍልስጤማውያን በበኩላቸው መሬታቸውን የመውሰድ ዘዴ አድርገው ይመለከቱታል።