ሳሌህ አል-አሩሪ

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል የሐማስ ምክትል መሪ የሆኑትን ሳሌህ አል-አሩሪ በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ በድሮን ጥቃት ገደለች።

እስራኤል የሐማስ መሪን ቤይሩት ውስጥ መግደሏ በሊባኖስ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት እንዳልሆነ ብትገልጽም ጠላቶቿ ግን የበቀል “ቅጣት” ይጠብቅሻል ሲሉ ዝተዋል።

የእስራኤል ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ከሆነ ሳሌህ አል-አሩሪ የተገደሉት “በተጠና መልኩ በተወሰደ እርምጃ” ነው።

ሐማስ ግድያውን ያወገዘ ሲሆን ሂዝቦላህ በበኩሉ በሊባኖስ ሉዓላዊነት ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ሲል ክስተቱን ገልጾታል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው እስራኤል “ሊባኖስን ወደ… ግጭት ለመክተት” እየሞከረች ነው ሲሉ ከሰዋል።

የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የሐማስ ምክትል የፖለቲካ መሪ አሩሪ በደቡባዊ ቤይሩት በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተገድለዋል። በጥቃቱ ሌሎች ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ሁለቱ የሐማስ ወታደራዊ አዛዦች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የቡድኑ አባላት ናቸው።

አሩሪ የሐማስ የጦር ክንፍ በሆነው በአልቃሳም ብርጌድ ውስጥ ቁልፍ ሰው ሲሆኑ የቡድኑ መሪ እስማኤል ሃኒያህ የቅርብ አጋር ነበሩ። ሊባኖስ ውስጥ በመቀመጥ በቡድናቸው እና በሂዝቦላ መካከል እንደ አገናን ድልድይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የእስራኤሉ ቃል አቀባይ ማርክ ሬጅቭ እስራኤል ግድያውን መፈጸሟን ባያረጋግጡም “ማንም ያድርገው ማን ይህ በሊባኖስ ግዛት ላይ የተቃጣ ጥቃት እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት” ሲሉ ለኤምኤስኤንቢሲ ተናግረዋል።

የሐመስ መሪ የተገደሉትበት ሕንጻ

መስከረም 26 የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ከሐማስ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ወዲህ የ57 ዓመቱ አሩሪ የተገደሉት ከፍተኛው የቡድኑ ኃላፊ ናቸው።

እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው ጥቃት አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ ከ22 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲል በጋዛ የሚገኘው እና በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።

በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሂዝቦላህ በርካታ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከማስወንጨፍ ባለፈ ከእስራኤል ጦር ጋር በርካታ ግጭቶች ውስጥ ገብቷል።

የሊባኖስ መንግስት የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ አሩሪ በደቡባዊ ቤይሩት በሚገኘው በሐማስ ጽህፈት ቤት ላይ በተፈጸመ የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መሞታቸውን ገልጿል።

ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሃሳቡን የሰጠ አንድ የዓይን እማኝ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እና የህክምና ባለሙያዎች አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ዙሪያ ተሰብስበው መመልከቱን ተናግሯል። የህንጻው ሦስተኛ ወለል ላይ መመታቱን አክሏል።

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተለቀቀ ቪዲዮ በተጨናነቀው የመኖሪያ አካባቢ በእሳት የተያያዘ መኪና እና በሕንፃዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ያሳያል።

የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ የሆኑት ሃኒያህ ጥቃቱን “አሳፋሪ… የሽብር ተግባር፣ የሊባኖስን ሉዓላዊነት የጣሰ እና የጦርነት ቀጠናው ለማስፋፋት ያለመ” ሲሉ ጠርተውታል።

ሂዝቦላህ የአሩሪ ሞት “በሊባኖስ፣ በህዝቦቿ፣ በደህንነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና በተቋሞቿ ላይ የተፈጸመ ከባድ ጥቃት ነው” ብሎ እንደሚቆጥረው ገልጿል።

ጥቃቱ “በጦርነቱ ሂደት ውስጥ አደገኛ ዕድገት የሚፈጥር ነው … እናም ሂዝቦላህ ይህ ወንጀል ያለ ምላሽ እና ቅጣት ፈጽሞ እንደማያልፍ እናረጋግጣለን” ብሏል።

የሐማስ እና የሄዝቦላ ዋነኛ ደጋፊ የሆነችው ኢራን የአሩሪ ግድያ ያለምንም ጥርጥር ሌላ የተቃውሞ ደም መፋሰሶችን እንደሚያቀጣጥል ተናግራለች።

የሊባኖሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ቡ ሀቢብ ለቢቢሲ ራዲዮ 4 እንደተናገሩት መንግስታቸው ከሂዝቦላህ ጋር እየተነጋገረ ነው። “ምላሽ እንዳይሰጡ ብንሠራም” ግን “እኛ ይህን አድርጉ አታድርጉ ብለን አንነግራቸውም። በዚህ ረገድ ከእነሱ ጋር እንነጋገራለን።”

በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ “ምላሽ ይስጡ ወይም አይስጡ” ግልጽ የሚሆን ይሆናል። አክለውም “ጉዳዩ በጣም ያሳስበናል። ሊባኖስ ወደ ጦርነቱ መግባት አትፈልግም። ሂዝቦላም መግባት አይፈልግም።”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሐማስ መሪዎችን ባሉበት ቦታ ሁሉ “እንደሚወገዱ” ከዚህ ቀደም ቃል ገብተዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ አሩሪ በዌስት ባንክ የሚገኘውን የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ከመሆን ባለፈ በአካባቢው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ይቆጣጠራሉ።

እአአ በ 2014 በዌስት ባንክ ሦስት እስራኤላውያን ታዳጊዎችን በማፈን እና በመግደል ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው ሪፖርቶች ገልጸዋል። በሌሎች ጥቃቶች ምክንያት ደግሞ በእስራኤል እስር ቤቶች ታስረውም ነበር።

ዘ እስራኤል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ በበኩሉ ከኢራን እና ከሂዝቦላ ጋር በጣም ጥብቅ ግንኙነት ካላቸው የሐማስ ባለስልጣናት አንዱ እንደነበሩም ዘግቧል።