
ከ 4 ሰአት በፊት
ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ የሚሰጠውን ስምምነት ኢትዮጵያ እና ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ሶማሊላንድ መፈራረማቸው ሶማሊያ በእጅጉ አስቆጥቷል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ለተፈራረሙትን የመግባቢያ ሠነድ ምላሽ ይሆን ዘንድ ሶማሊያ በአዲስ አበባ ያሉ አምባሳደሯን ወደ ሞቃዲሹ ጠርታለች።
የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወመዋለን ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ በበኩላቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ የሶማሊያ ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “የሶማሊ ሕዝብ እንዲረጋጋ አሳስባለሁ፤ አንድ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው አገራችንን እንደምንከላከል ነው። የትኛውም መሬታችን፣ የባሕር ወይም የአየር ክልላችን አይጣስም። በየትኛውም ሕጋዊ አማራጭ እንከላከላለን።” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ጨምረውም “በሰሜንም ይሁን በደቡብ ባለው ሕዝባችን ድጋፍ አገራችንን መከላከል እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።
ሶማሊላንድ እአአ 1991 ላይ ከሶማሊያ ተነጥላ ሉዓላዊት አገር መሆኗን ብታውጅም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የትኛውም አገር እውቅና አልሰጣትም።
አፍሪካ ሕብረት ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ በሆነችው ኢትዮጵያ እውቅና ማግኘት ለሶማሊላንድ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ሊሆን የሚችለውም ለዚህ ነው።
- የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም አለ2 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አመለከቱ2 ጥር 2024
- ሶማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠራች2 ጥር 2024
አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር እስካሁን ድረስ በሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ መካከል በሕግ የሚጸና ስምምነት አልተካሄደም።
በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተፈረውም የመግባቢያ ሠነድ ወደፊት ለሚደርሱት ስምምነት መደራደሪያ የሚሆናቸው መነሻ ነጥብ ነው።
የመግባቢያ ሠነድ ከተፈረመ በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ንግግር ተደርጎ ስምምነቱ በአንድ ወር ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረግበት ቀጠና ብዙ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ምንም ጥያቄ የለውም።
ይሁን እንጂ የ120 ሚሊዮን ሕዝባ ባለቤት ለሆነችው ወደብ አልባ አገር የባሕር ጠረፍ መስጠት ለአዲስ አበባ እና ለጎረቤት አገራት ምን ማለት ነው?
ኢትዮጵያ
ከባሕር ለሚዋሰኑ አገራት 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ ትልቅ ላይመስል ይችላል። በዓለም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ኖሯት የባሕር በር ለሌላት እና ለወጪ ገቢ ምርቶቿ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ለምትከፍለው ኢትዮጵያ ግን 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ ትልቅ ዋጋ አለው።
ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ገቢ ምርቶቿን የምታንቀሳቅሰው 31 ኪሎ ሜትር በተዘረጋው የጂቡቲ ወደብ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት ወር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት “የሕልውና ጉዳይ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ጽኑ የሆነ ፍላጎትን የምታሳየው ለባሕር ላይ ንግድ ብቻ ላይሆን ይችላል። አገሪቱ በአንድ ወቅት በምጽዋ እና አሰብ ላይ የባሕር ኃይል ባለቤት ነበረች።
ይሁን እንጂ ኤርትራ እአአ 1993 ከኢትዮጵያ ተለይታ ነጻ አገር ስትሆን፣ኢትዮጵያ ወደቦቿን እና የባሕር ጠረፏን አጣች።

ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን መመለስ ለምን አስፈለጋት?
የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሠነድ የፈረመችበት ዋነኛ ምክንያት የባሕር ላይ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ለመገንባት ፍላጎት ስላላት ነው ይላሉ።
አምባሳደር ዴቪድ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ወይም በኤደን ባሕረ ሰላጤ የባሕር ኃይል መገንባት ትፈልጋለች።
“ሶማሊላንድ በኤደን ባሕረ ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ በሊዝ ትሰጣለች ኢትዮጵያም [ጦር ሰፈር] ታቋቁማለች። እንዲሁም ሶማሊላንድ ምርቶችን የምትልከበት እና የምታስገባበትን በርበራ ወደብን ኢትዮጵያ ልትጠቀም ትችላለች። ይህ ግን (የስምምነቱ) ዋነኛ ዓላማ አይመስለኝም። ወታደራዊ ወይም የባሕር ኃይል ለመመስረት ካለ ፍላጎት የመጣ ይመስለኛል።” ብለዋል።
በአትላንቲክ ካውንስል አፍሪካ ሴንተር ባልደረባ የሆኑት ማይክል ሹርኪን ደግሞ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ከፍታ ከማግኘት ይልቅ ሶማሊያን ቢያስቆጣም የተሻለ ያለችውን አማራጭ ወስዳለች ይላሉ።
ማይክል ኢትዮጵያ ለባሕር በር ስትል ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ለሶማሊላንድ የሚገባትን እውቅና መስጠትን መርጣለች ይላሉ።
“ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ጽኑ ፍላጎት አላት” የሚሉት ማይክል፤ የባሕር በር ለማግኘት ሲባል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ቀድሞ ከግምት በማስገባት የተወሰደ አማራጭ ነው ይላሉ።
“እውነት ነው ይህ ይህ ሶማሊያን ሊያስቆጣ ይችላል፤ ነገር ግን ከኤርትራ ጋር ጸብ ውስጥ ከመግባት ያነሰ አደጋ አለው” ብለዋል።
ሶማሊያ
ጎምቱ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ይህ ክስተት የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና መረጋጋት ሊያደፈርሰው ይችላል ይላሉ።
የመግባቢያ ሠነዱ መፈረም የተሰማው ደግሞ ሶማሊያና ሶማሊላንድ ንግግር ለመጀመር መስማማታቸው በተሰማ ማግስት ነው።
ሶማሊያና ሶማሊላንድ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለመነጋገር መስማማታቸው መዘገቡ ይታወቃል።
በሶማሊላንድ የሶማሊያ ልዩ ልዑክ አብዱልከሪም ሑሴን ጉሌድ እንደሚሉት ይህ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ ‘ዓለም አቀፍ ደንቦች ፍጹም ቸል ያለ ወይም ደግሞ ከመጤፍም ያልቆጠረ’’ ነው ካሉ በኋላ በሞቃዲሾና በሐርጌሳ መካከል የተጀመረውን መልካም ጅምር ከመሠረቱ የሚንድ ሲሉ ተችተዋል።
የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፈርማጆ በበኩላቸው በኤክስ ገጻቸው የመግባቢያ ሠነዱን “ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ አሳሳቢ” ነው ብለዋል።
ጨምረውም ‘’ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ማክበር ለአካባቢያዊ ሰላም መረጋገጥ መሠረት ነው፤ [የተጣሰውም ይህ ነው] በመሆኑም የሶማሊያ መንግሥት የተመጣጠነ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል።
መሐመድ ሙባራክ የቀድሞ የሂራል ኢንስቲትዩት ኃላፊ ናቸው። ሒራል በጸጥታ ጉዳዮች የቲንክ ታንክ ተቋም ነው። መሐመድ ሙባራክ እንደሚሉት ከሆነ ነገሮች እየከረሩ ከመጡ ኢትዮጵያ በደቡባዊ ሶማሊያ የሚገኙትን ወታደሮቿን ልታስወጣ ትችላለች። ይህ ደግሞ ሌላ የሰላምና ደኅንነት ራስ ምታት ይፈጥራል” ብለዋል።
መሐመድ ሙባራክ እንደሚያስታውሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለወራት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያሻት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር። አሁን የሆነውም ሌላ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲሉት የነበረውን ነገር ነው።
“ዐቢይ ያሉትን ለማሳካት ማንኛንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፤ እርምጃው የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት የሚያናጋ ቢሆንም” ይላሉ።

ኬንያ
የወደብ ጉዳይን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ንግግር ላይ ከነበሩ አገራት አንዷ ኬንያ ናት። ባለፈው ነሐሴ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላሙ ወደብን ጎብኝተው ነበር። ይህ በግንባታ ላይ ያለው ወደብ ኬንያን ጨምሮ ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።
ላሙ ወደ ሥራ ሲገባ ኬንያ ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ገቢ ሸቀጦች የምታገኘውን የወደብ ትርፍ መሻማቷ አይቀሬ ነው። የዓለም ባንክ ኬንያ በላሙ 15 ከመቶ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎት ከጂቡቲ ልትወስድ እንደምትችል ይተነብያል።
ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድም ይሁን ከሌላ አገር የወደብ ስምምነት ስታደርግ ኬንያ በላሙ መዘግየት የተነሳ ገቢዋን እያጣችው እንደሆነ ይቆጠራል።
በፈረንጆቹ 2020 ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለአጭር ጊዜም ቢሆን አቋርጣው ነበር። ይህም የሆነው የሶማሊላንዱን መሪ ሙሴ ቢሂን በማስተናገዷ ነበር።
ኬንያ ለሶማሊላንድ እውቅና የምትሰጠው በሶማሊያ ውስጥ እንዳለች አንድ የአካባቢያዊ መንግሥት ነው። ሆኖም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኬንያም በሐርጌሳ ቆንጽላ ቢሮ አላት።
ግብጽ
ግብጽ በቀይ ባሕር ዳርቻ በርካታ ወደቦች ያሏት በአካባቢው ቁልፍ ሚና ያላት አገር ናት።
ስምንት የንግድ ወደብ እና አምስት የፔትሮሊየም፣ የማዕድን እና የቱሪስት ወደቦች አሏት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀይ ባሕር የባሕር በር ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ለግብጽ ምቾት የሚሰጥ ጉዳይ አይመስልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ‘’የሕልውና ጉዳይ’’ ሲሉ ነው የሚገልጹት።
ተንታኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዳሴ ግድብ ግንባታን በመቀጠል ላይም ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው ነው የሚናገሩት። የሕዳሴ ግድቡ ለግብጽ ምቾት የሚነሳ ጉዳይ ነው። የ1929 ስምምነት የናይል ወንዝን ውሃ ሙሉ መብት ለግብጽና ሱዳን የሚሰጥ ነበር።
አሁን ግን በግድቡ ግንባታና አጠቃቀም ጉዳይ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋ አንዳች ስምምነት ላይ ለመድረስ እየጣረች ነው።
አሁን ኢትዮጵያ በበርበራ የባሕር በር ካገኘች በዚያ አካባቢ ካሉ ኃያላን አገሮች ተርታ (ግብጽን ጭምሮ) በነሱ ቁመና ሊያሰልፋት የሚችል ነው። አገሮቹ በቀይ ባሕር የባሕር በር በማግኘታቸው ኢኮኖሚያቸውን በአያሌው ማሳደግ የቻሉ ናቸው።

ጂቡቲ
የአፍሪካ ትንሸ አገር ጂቡቲ ወደ ሱዊዝ ቦይ መግቢያ በር ተደርጋ ትወሰዳለች። ስዊዝ ቦይ በዓለም ካሉ የመርከብ ጉዞ እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው የባሕር ጎዳናዎች አንዱ ነው። ጂቡቲ ወደብ አገልግሎት ለኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት ነው። ሥራ በመስጠትም ሆነ ትልቅ ገቢ ለመንግሥት በማስገኘት ሁነኛውን ቦታ የሚይዘው ይኸው የወደብ አገልግሎት ነው። ጂቡቲ ያለ ወደቧ ባዶ ናት።
ወደቧ ትልቁን አገልግሎት የሚሰጠው ለትልቅ ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ሌላ የወደብ ስምምነት ማድረጓ ጂቡቲን ማሳሰቡ የማይቀር ነው።
ቻይና
ቻይና ይህ ጉዳይ ግድ ሊላት የሚችለው ከታይዋን ጋ በተያያዘ ነው። ታይዋን ለቻይና ከቤት ያፈነገጠች ቤተሰብ ናት። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ትመለሳለች ብላ ነው የምታስበው። ሶማሌላንድ ከታይዋን ድጋፍ ታገኛለች። ቻይና በአንጻሩ ሶማሊያን ትደግፋለች።
በ2020 ሶማሊላንድና ታይዋን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መጀመራቸው ቻይናን አስቆጥቶ ነበር። ሁለቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የላቸውም። ሁለቱም በጎረቤቶቻቸው ቻይናና ሶማሊያ ራሳቸውን የቻሉ አገራት እንዳልሆኑ ይነገራቸዋል።