የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ከግብጽ አቻቸው ጋር (ፋይል ፎቶ)
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ከግብጽ አቻቸው ጋር (ፋይል ፎቶ)

ከ 1 ሰአት በፊት

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ራሷን ከሶማሊያ ገንጥላ ነጻ አገር መሆኗን ብታውጅም፤ እስካሁን ደረስ ከየትኛው ሀገር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋም እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን እውቅና አላገኘችም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ይህን የጋራ የመግባቢያ ሠነድ ታሪካዊ ሲሉ ቢገልጹትም በሶማሊያ በኩል ጠንካራ ትችት ተሰንዝሮበታል።

የሶማሊያ መንግሥት ሶማሊላንድ የፌደራል መንግሥቱ አንድ አካል መሆኗን ገልጾ፤ ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎታል።

ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት ተመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ የአረብ ሊግ፣ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕጎች ተገድባ እንድትቆይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ይህን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከግብጽ ፕሬዝዳንት እና ከኳታር መሪ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

የግብጽ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አሕመድ ፋሚ ሁለቱ መሪዎች በስልክ በነበራቸው ውይይት ላይ አል-ሲሲ “ግብጽ ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” ገልጸዋል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም “የሶማሊያን ደኅንነት እና መረጋጋት ለመደገፍ” ግብጽ ድጋፍ እንደምታደርግ አል-ሲሲ በስልክ ውይይቱ ወቅት መናገራቸውን፣ እንዲሁም ሁለቱ መሪዎች “በቀጠናው ስላሉ ለውጦች” እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከኳታሩ ኢሚር ተሚም ቢን ሐማድ ጋር መነጋገራቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ ቀጠናዊ ግንኙነቶች ላይ መወያየታቸውን ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት የስምምነቱን መፈረም አስመልክቶ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የፌደራል ሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊያ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተሮች መሠረት የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ጠቃሚ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን ብሏል።

የሕብረቱ ቃል አቀባይ በኩል ትናንት የወጣው መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋገትን ለማስፈን የሶማሊያ ሉዓላዊነትን ማክበር ቁልፍ ነው ብሏል።