ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

3 ጥር 2024, 17:04 EAT

ተሻሽሏል 3 ጥር 2024, 17:04 EAT

የኢትዮጵያ መንግስት ለሶማሊላንድን ዕውቅና መስጠትን በተመለከተ አቋም ለመያዝ መስማማቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊላንድን ዕውቅና ማግኘት በተመለከተ ጉዳዩን “በጥልቀት አጢኖ አቋም ለመውሰድ” መስማማቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ረቡዕ 24/2016 ባወጣው መግለጫ በቅርቡ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት “ማንንም የሚጎዳ አይደለም፤ ሕግም አልተጣሰም” ብሏል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ታህሳስ 22፤ 2016 ዓ.ም. በጋራ ለመሥራት ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

መግለጫው ስምምነቱ “የሁለቱንም ወገኖች ታሪካዊ ጥያቄዎች የሚመልስ” መሆኑንም ገልጿል።

ሁለቱ መንግስታት በአዲስ አበባ ከተማ የተፈራረሙት የስምምነት ሰነድ “ለኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት የምታኝበትን ዕድል የሚያስገኝ” መሆኑን ዛሬ ዕኩለ ቀን በወጣው መግለጫ ላይ ተመላክቷል።

ሶማሊላንድ ደግሞ “ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ” እንደሚኖራት በመግለጫው ሰፍሯል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አግልግሎት የዛሬውን መግለጫ የጀመረው የሶማሊላንድን የቅኝ ግዛት እና ደህረ ቅኝ ግዛት ታሪክ በማተት ነው።

መግለጫው ከአውሮፓውያኑ 1991 ወዲህ ሶማሊላንድ “ነጻነቷን አውጃ በተከታታይ ሰላማዊ ምርጫ ሰከን ያለ የመንግስት ቅይይር በማካሄድ ላይ ለ30 ዓመታት ዲሞክራሲን በመለማማድ ላይ ትገኛለች” ሲሉ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችውን ሶማሊላንድ አሞግሷታል።

ራስ ገዝ አስተዳደሯ እስካሁን እውቅና አለማግኘቷን ያስታወሰው መግለጫው ይህ ቢሆንም ግን “የወደብ አገልግሎትና ልማትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት ፈርማለች” ሲል የትላንት በስቲያው ስምምነት የመጀመሪያዋ አለመሆኑን አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት በሐርጌሳ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ከፍታው እንደሚንቀሳቀሱ የጠቆመው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል ቆየት ያለ የትብብር ስምምነት እንደነበር አስታውሷል።

ሰኞ ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የተፈራረሙት ስምምነት ይህኑ ወዳጅነት ለማጠናከር የተደረገ ጥረት አካል መሆኑን መግለጫው አክሏል።

በተጨማሪም ስምምነቱ ፤ “የሁለቱንም ወገኖች ታሪካዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን በሚመልስ፥ ዝርዝር፥ ግልጽ እና ስትራቴጂክ አጋርነትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ነው” ብሎታል።

መግለጫው “በሶማሊላንድ በኩል ማንም አገር እየፈለገ ሊከውናቸው የማይችሉ ጥያቄዎቻቸውን የሚመልስ ሲሆን ከማንም ሀገር ሊያገኙ የማይችሉትን እገዛና ሽርክና ያጎናጽፋቸዋል” ሲል ሶማሊላንድ ከስምምነቱ የምታገኘውን ጥቅም አብራርቷል።

ይህ የሁለቱ መንግስታት ስምምነት የሶማሊያ መንግስትን ክፉኛ አስቆጥቶ የሀገሪቱ ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ አስገድዶታል።

ከዚህ አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር አብዱላሂ ዋርፋን ወደ ሞቃዲሾ ጠርቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ መንግስታት ስምምነት “ህጋዊ መሰረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው” ብሎታል። የሶማሊያ መንግስት ይህን ይበል እንጂ ኢትዯጵያ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም የተጣሰ ህግና የተሰበረ እምነትም የለም” ብሏል።

በርበራ ወደብ

በተያያዘ ዜና የምስራቅ አፍሪካ መንግሥታት በይነ መንግሥት [ኢጋድ] ባወጣወ መግለጫ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል “የተፈጠረው አለመግባባት እንዳሳሰበው” ገልጧል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ወርቅነህ ገበየሁ [ዶ/ር] ሁኔታውን እየተከታተሉት እንዳለና ሁኔታው በቀጣናው መረጋጋት ላይ የሚያመጣውን ጫና እንደሚረዱ መግለጫው ያትታል።

ሁለቱ እህትማማች ሃገራት በኢጋድ መርሕ መሠረት ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መግለጫውን ጥሪ አቅርቧል።

ይህን የኢጋድ ማሳሰቢያ ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ ያወጣ ሲሆን “የሶማሊያ መንግሥት በኢጋድ መግለጫ እንዳልተደሰተ መግለጥ ይወዳል” ብሏል።

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያወጣው መግለጫ “ኢጋድ የኢትዮጵያ መንግሥት የሶማሊያ መንግሥትን ሉዓላዊነት የተጋፋበትን ድርጊት አልኮነነም” ሲል የበይነ መንግሥታቱን ድርጅት ወቅሷል።

“የሶማሊያ መንግሥት የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ያወጡትን መግለጫ ይቃወማል። መግለጫው ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደላ እንደሆነ ያምናል። ዋና ፀሐፊው ይቅርታ ጠይቀው መግለጫውን ሰርዘው ትክክለኛ እርምጃ ይወስዳሉ ብለን እናስባለን።”

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡትን ስምምነት ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረትም መግለጫ ያወጣ ሲሆን “የሶማሊያን ሉዓላዊነት ማክብር አስፈላጊ ነው” ብሏል።