
ከ 9 ሰአት በፊት
በኢራኑ ጀኔራል ቃሲም ሱሌማኒ አራተኛ ሙት ዓመት ላይ የመቃብር ስፍራ አካባቢ በፈነዱ ሁለት ቦምቦች ቢያንስ 103 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቃሲም ሱሌማኒ በአሜሪካ ከተገደሉ አራተኛ ዓመታቸው ነው።
ኢሪብ የተሰኘው የሀገሪቱ ብሄራዊ ጣቢያ፤ ፍንዳታው በደቡባዊ ከርማን ከተማ ሳህብ አል-ዛማን መስጊድ አቅራቢያ ሰልፈኞችን ሲመታ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
የከርማንን ምክትል ገዥን የጠቀሰው ዘገባው ፍንዳታውን “የሽብር ጥቃት” ነው ብሏል።
ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጎዳናዎች ላይ የወዳደቁ አስከሬኖችንና አምቡላንሶች ወደ አካባቢው ሲገሰግሱ አሳይተዋል።
ከፍንዳታው ጀርባ ማን እንደለ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ከየትኛውም ቡድን የኃላፊነት መግለጫ ወዲያው አልወጣም።
ሆኖም የአረብ ተገንጣይ የሆኑ ቡድኖች እስላሚክ እስቴት (አይኤስ) እና የሱኒ ጅሃዲስት ቡድን በቅርብ ዓመታት በጸጥታ ኃይሎች እና በቅዱስ ስፍራዎች ላይ ከባድ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ይታወሳል።
ቃሲም ሱሌማኒ ከጠቅላዩ መሪ አያቶላ አሊ ኪማኒ በመቀጠል በኢራን ጉምቱ መሪ ተደርገው ይታዩ ነበር።
ሱሌማኒ እ.አ.አ በ2020 በጎረቤት አገር ኢራቅ በአሜሪካ የድሮን ጥቃት ነው የተገደሉት።
- እስራኤል የሐማስ ምክትል መሪን ሳሌህ አል-አሩሪን ቤይሩት ውስጥ ገደለች3 ጥር 2024
- እስራኤል በጋዛ የተጀመረው ጦርነት በአዲሱ የፈረንጆች ዓመትም ይቀጥላል አለች1 ጥር 2024
- ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሰው ሐማስ የገንዘብ ምንጩ ምንድን ነው? ድጋፍ፣ ግብር፣ ክሪፕቶከረንሲ . . .?16 ታህሳስ 2023
ፍንዳታው በኢራን የሚደገፈው ሀማስ ምክትል መሪ የነበሩት ግለሰብ ሌባኖስ ውስጥ በእስራኤል የድሮን ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረት በነገሰበት ወቅት የተከሰተ ነው።
በኢራን ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ የተላለፈ ምስል በጀኔራሉ የትውልድ ከተማ ከርማን አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰባስበው እንደነበር አሳይቷል።
የቴሌቭዥን ጣቢያው በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 8፡50 ገደማ ከጄኔራሉ መቃብር 700 ሜትር አካባቢ የመጀመሪያው ፍንዳታ መከሰቱን አስታውቋል።
ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ ከ15 ደቂቃ በኋላ ከመቃብር ስፍራው በአንድ ኪ/ሜ ርቀት ላይ መፈጸሙ ተነግሯል።
ለኢራን አቢዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ታስማኒ የዜና አገልግሎት ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ቦምቦቹ በሪሞት ተጠምደው መፈንዳታቸውን ዘግቧል።
አንድ የአይን እማኝ “ወደ መቃብር ስፍራው እያመራን ነበር፤ ከኋላችን የነበረ ተሽከርካሪ በድንገት ቆመ እና ቦምብ የያዘው የቆሻሻ ማጠራቀሚያው ፈነዳ” ሲሉ ሁነቱን ገልጸዋል።
የአገሪቱ ብሄራዊ ጣቢያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ጠቅሶ በፍንዳታዎቹ 103 ሰዎች መገደላቸውንና 141 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።
አብዛኞቹ የቆሰሉት ሰዎች በከባድ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውንም ባለስልጣናቱ አክለው ተናግረዋል።
የኢራን ቀይ ጨረቃ ህክምና ለመስጠት ወደ መጀመሪያው ፍንዳታ ስፍራ ያመራ አንድ የህክምና ባለሞያ በሁለተኛው ፍንዳታ ህይወቱ እንዳለፈ አስታውቋል።
ምስሎች በጥቃቱ የሱሌማኒ መቃብር ጉዳት እንዳልደረሰበት አሳይተዋል።
ቃሲም ሱሌማኒ በኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥነታቸው ዘመን ኩድስ የተባለው የውጭ ተልዕኮ ቡድን መሪና የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀያሽ ነበሩ።