የደብረ ብርሃን ካርታ

3 ጥር 2024, 17:43 EAT

በደብረ ብርሃን ከተማ ረቡዕ ከንጋት እስከ ቀኑ አጋማሽ የቆየ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን የከተማዋ ከንቲባ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ እንቅስቃሴ መቆሙን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን በደብረ ብርሃን በሚገኙ የባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪዎች ላይም ለሁለት ቀናት የሚቆይ እገዳ ተጥሏል።

ከአዲስ አበባ ከተማ 130 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ ረቡዕ ታህሳስ 24፤ 2016 ዓ.ም “በተለያዩ አቅጣጫዎች” የተኩስ ልውውጥ መሰማት የጀመረው ከጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ጀምሮ መሆኑን ሶስት የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በከተማዋ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ለቢቢሲ ያረጋገጡ ሲሆን ዝርዝር መረጃ ግን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በከተማዋ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ የነበረው “አልፎ አልፎ” እንደነበር የሚናገሩት ተቀዳሚ ከንቲባው፤ በአሁኑ ሰዓት ይህ ተኩስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

አቶ በድሉ የተኩስ ልውውጡ በማን መካከል እንደተደረገ ባይገልጹም ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች የተኩስ ልውውጥ የተካሄደው በክልሉ በሚንቀሳቀሱት የፋኖ እና በአማራ ክልል የአድማ ብተና ኃይሎች መካከል እንደሆነ ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ በበኩላቸው ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱን ጠቅሰዋል።

በከተማዋ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት ማለፉን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ “በተለይ ኡራኤል አካባቢ እና በአንኮበር መስመር ላይ የተኩስ ልውውጦች ነበሩ። በእሱም በተባባሪ ጥይት የተወሰኑ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “ሁለት ወይም ሶስት” ሰዎች ስለመሞታቸው “መረጃው እንዳላቸው” ተናግረዋል።

ይሁንና ቢቢሲ የሰዎች ህይወት ስለማለፉ ከሌላ አካል አላረጋገጠም። ቢቢሲ የሰው ህይወት ስለማለፉ ከከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ እንዲሁም ከደብረ ብርሃን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎቹ እንደሚያስረዱት የተኩስ ልውውጡ የተካሄደው በተለያዩ የከተማዋ መግቢያ አካባቢዎች ላይ ነው።

በሶስት አቅጣጫዎች ተኩስ እንደነበር የሚናገሩ አንድ የከተማዋ ነዋሪ “[የተኩስ ልውውጥ የተካሄደባቸው] በከተማዋ መግቢያ የሚገኙ አካባቢዎች ናቸው። በማረሚያ ቤት በኩል ያለው አካባቢ ወደ ደሴ መውጫ ነው። [ሌላኛው ተኩስ የተሰማበት] አንሳስ ማርያም ወደ አንኮበር መውጫ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ወደ መራቢቴ መውጫ ነው። በእነዚህ አቅጣጫዎች ተኩስ ነበር” ብለዋል።

“ማረሚያ ቤት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት እኚህ ግለሰብ፤ በዚህ አካባቢ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ገልጸዋል።

ሌላ የከተማይቱ ነዋሪ በበኩላቸው ተኩስ የነበረው “ዙሪያውን” እንደሆነ በመጥቀስ ተመሳሳይ ሐሳብ አንስተዋል።

እንደ ነዋሪው ገለጻ ኡራኤል፣ አንኮበር መውጫ እንዲሁም 02፣ 03 እና 08 አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሶሰት ነዋሪዎች እንደሚገልጹት የተኩስ ልውውጡ ከጠዋት ጀምሮ የተሰማ ቢሆንም ተኩሱ በየመሃሉ ጋብ የሚልባቸው ጊዜያት ነበሩ።

አንድ ነዋሪ፤ “[ተኩሱ] በየጊዜው የሚነሳ አይነት ነው። ግን ሲጀምር ደግሞ ምልልስ ያለው አይነት ነው። የተፋዘዘ ነገር ሳይሆን ቆየት ብሎ ይነሳል ግን በጣም ‘አክቲቭ’ የሆነ ድባብ አለው” ሲሉ የተኩስ ልውውጡ በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ የተሰማው ይህ የተኩስ ልውውጥ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ መቆሙን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ ግን እስካሁን ድረስ መቆሙን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ባንኮች፣ መደብሮች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን ሶስቱም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የከተማዋ ኮማንድ ፖስት በባለ ሶሰት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።

ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ እስከ ነገ ሐሙስ ታህሳስ 25፤ 2016 ድረስ የሚቆይ መሆኑን የገለጸው የከተማ አስተዳደሩ፤ “የባጃጅ አሽከርካሪዎች በተጠቀሱት ቀናቶች ከማሽከርከር ወይም ከእንቅስቃሴ እንድትቆጠቡ እንገልጻለን” ሲል አሳስቧል።