ሐርጌሳ ከተማ
የምስሉ መግለጫ,ሐርጌሳ ከተማ

3 ጥር 2024, 10:43 EAT

ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የምትገኝ ከፊል በረሃማ የሆነች አካባቢ ናት።

የሶማሊያ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ሲያድ ባሬ እኤአ በ1991 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነጻ አገር መሆኗን አውጃለች።

ይህ ውሳኔ የተሰማው በሲያድ ባሬ አገዛዝ ዘመን ነጻነታቸውን ለማግኘት ሽምቅ ውግያ ሲያካሄዱ የነበሩ ታጣቂዎች ረዥም የትጥቅ ትግል ካደረጉ በኋላ ነው።

በዚህ የሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ ከተሞች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

ምንም አንኳ ከየትኛውም የዓለም አገር እውቅና ባታገኝም ሶማሊላንድ የራሷ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይል እንዲሁም የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።

ከዚህ ቀደም በታሪኳ ዘለግ ላለ ጊዜ በእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ሥር የነበረችው ሶማሊላንድ በሶማሊያ የሚካሄደውን ጦርነት፣ ግጭት ሁሉ ማምለጥ ችላለች።

ስለ ሶማሊላንድ በጥቂቱ

የሶማሊላንድ ዜጋ ከሐርጌሳ አቅራቢያ የግመል ወተት ሲጠጣ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊላንድ ዜጋ ከሐርጌሳ አቅራቢያ የግመል ወተት ሲጠጣ

በ7ኛው ክፍለዘመን- ወደ አሁኗ ሶማሌላንድ እስልምና እግሩን አስገባ።

በ14ኛው ክፍለ ዘመን- በእስላማዊ ሱልጣኖች ተይዞ የነበረው ስፍራ በኢትዮጵያ ንጉሥ እጅ ወደቀ

1527- የአዳል ሱልጣን በኢትዮጵያ ንጉሣዊ አስተዳደር ላይ በማመጽ ጦር ካዘመተ በኋላ ኢትዮጵያ በ1543 በፖርቹጋሎች እገዛ ማሸነፍ ችላለች።

1888- እንግሊዝ ከአካባቢው ሱልጣኖች ጋር በመስማማት የሞግዚት አስተዳደር መሠረተች።

1899- ሞሐመድ አብደላህ በብሪቴይን ላይ በማመጽ እስከ 1920 ድረስ ውግያ ተካሄደ።

1960- የብሪቴይን ሶማሌላንድ እና የጣልያን ሶማሌላንዶች ነጻ ሆነው ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ጋር ተዋሀዱ።

1991- የቀድሞ የብሪቴይን ሶማሌላንድ ግዛት የሲያድ ባሬን ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ ሶማሌላንድ ነጻ አገር መሆኗን አወጀች።

2001- ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ በ1997 የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት በማጽደቅ ሶማሌላንድ ነጻ አገር መሆኗን አረጋገጠ።

2016- ሶማሌላንድ ምንም እንኳ የትኛውም የዓለማችን አገራት ነጻ አገር መሆኗን ባይቀበሉትም፣ የተመሠረተችበትን 25ኛ ዓመት የነጻነት በዓል አክብራለች።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ

የራስ ገዟ አገር ሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ናቸው።

ሙሴ ቢሂ አብዲ በኅዳር ወር፣ 2017 ዓ/ም ተመርጠው ሥልጣን ላይ ሲወጡ የተኩት አህመድ ሲላንዮን ነበር።

ፕሬዝዳንት ቢሂ የገዢው ፓርቲ ኩልሚዬ ፓርቲ ከ2010 ጀምሮ ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ ነው።

ጡረተኛው የአየር ኃይል ፓይለት ቢሂ በ1990ዎቹ የሶማሌላንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የፕሬዝዳንት ቢሂ የሥልጣን ዘመን በኅዳር ወር 2022 ከማለቁ በፊት የምርጫ ቦርድ በገንዘብ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ምርጫውን በማራዘሙ፣ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት የሥልጣን ዘመናቸውን ለሁለት ዓመት ያህል አራዝመውላቸዋል።

ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ዋዳኒ እና ዩሲአይዲ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርገው እንደማይቀበሏቸው አሳውቀዋል።

በወቅቱ የነበረው ተቃውሞ እና ሕዝባዊ አመጽ የተረጋጋች የነበረችውን ራስ ገዟን ሶማሌላንድ ጸጥታ አደጋ ላይ ጥሎት ነበር።

ሶማሊላንድ የራሷ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይል እንዲሁም የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።

በሶማሌላንድ የመንግሥት አፈ ቀላጤ ሆኖ የሚያገለግለው ራዲዮ ሐርጌሳ ሲሆን በይፋ ፈቃድ ያገኘ በአገሪቱ የሚገኝ ብቸኛው ሬድዮ ጣብያ ነው።

በርግጥ ከመንግሥት ቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣብያ ጎን ለጎን የሚሠሩ የግል ቴሌቪዥን ጣብያዎች ይገኛሉ።

መንግሥትን የሚተቹ መገናኛ ብዙኀን እና ጋዜጠኞች፣ ከጎረቤት ፑንትላንድ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ የሚዘግቡትን ጨምሮ በመንግሥት ወከባ ይደርስባቸዋል።