ሔለን ተስፋዬ

January 3, 2024

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አገሮች የሚሳተፉበት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የአርብቶ አደሮች ኤክስፖ በቅርቡ እንደሚካሄድ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከኢጋድ ጋር በመተባበር ከጥር 17 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚቆይ ኤክስፖ መሆኑን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ማክሰኞ ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዚህ ኤክስፖ የኢጋድ አባል አገሮች ልዑካኖቻቸውን በመላክ የሚሳተፉ መሆኑንና የቀጣናውን ትስስር የሚያጠናክሩ የልምድ ልውውጦች እንደሚደረጉ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) አስታውቀዋል፡፡

በተለይ አርብቶ አደሮችን የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች እንደሚከናወኑና የአርብቶ አደሮች አካባቢ የልማት ፀጋዎችን ለማልማት የሚከናወኑ ሥራዎች ጭምር እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

የአርብቶ አደሮችን የሕይወት ዘይቤ የሚያቃልሉ የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ፈጠራዎች በኤክስፖው የሚቀርቡ መሆኑን የጠቆሙት አይሻ (ኢንጂነር)፣ በርካታ የባለሙያዎች ጥናትና የልምድ ልውውጦች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች ኤክስፖ ከአርብቶ አደሮች ጋር የሚሠሩ ልማት አጋሮች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የምርምር የፈጠራና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

ለተከታታይ ሰባት ቀናት በሚካሄደው ኤክስፖ የኢትዮጵያም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አርብቶ አደር አካባቢዎች ዕምቅ ፀጋዎች ጎልተው የሚታዩበት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸውና የኑሮ ዘይቤዎቻቸው የሚተዋወቁበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ትልቁን ድርሻ የሚሸፍነው ቆላማው አካባቢ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአካባቢው ያለው ዕምቅ የከርሰ ምድር የውኃ ሀብት፣ ማዕድናትና ሌሎች ፀጋዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የፖሊሲና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል በቅርቡ ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ለአብነት አውስተዋል፡፡ ይህም በዘርፉ ያሉትን የሕግ ክፍተቶች ለመሙላትና በዘላቂነት ለማልማት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ኤክስፖው ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የቆየው 19ኛው ‹‹የአርብቶ አደሮች ቀን››፣ ዘንድሮ ከፍ ባለና ቀጣናዊ ትስስር በመፍጠር ለማክበር ከኢጋድ ጋር ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል፡፡