

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም
ዜና የአማራ ክልል የይቅርታ ቦርድ ለ2,741 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
ቀን: January 3, 2024
የአማራ ክልል የይቅርታ ቦርድ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ 2,741 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም እንዳስታወቁት፣ ቦርዱ ቀደም ሲል በይቅርታ ከማረሚያ ቤት ወጥተው የነበሩና ሦስት ዓመታት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ 38 ግለሰቦች የተሰጣቸው ይቅርታ ተነስቶ በሕግ እንዲጠየቁ ወስኗል።
የቢሮ ኃላፊው ቦርድ አክለውም፣ ቦርዱ ይቅርታውን ማድረግ የቻለው በቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ያመጡና የቆይታ ጊዜያቸውን በአብዛኛው ማጠናቀቃቸውን በማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ቦርዱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ 2,741 ታራሚዎች መሥፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው በይቅርታ እንዲለቀቁ ሲወስን፣ በሽብርተኝነት፣ በአስገድዶ መድፈር፣በሙስና፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና በመሠረተ ልማት ማውደም ተከሰው የተፈረደባቸውን እንደማያካትት ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።
የተሰጠው ይቅርታም ማረሚያ ቤት ውስጥ ምሥጉን መሆን የሚያስገኘውን ዕድል ለማሳየትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለማመላከት መሆኑን አክለዋል።
ቀደም ብሎ ወንጀል ፈጽመው የነበሩና በይቅርታ የተለቀቁ ግለሰቦች ሦስት ዓመት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል በመፈጸማቸው፣ የተሰጣቸው ይቅርታ ተነስቶ በሕግ እንዲጠየቁ መወሰኑንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል። ይቅርታ የተሰጠው ግለሰብ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀል የበደለውን ማኅበረሰብ መካስ እንጂ ተመልሶ ወደ ጥፋት መግባት ለተደጋጋሚ የሕግ ተጠያቂነት የሚያጋልጥ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሆነም አክለዋል፡፡