ዜናበአርባ ምንጭ የተከሰተውን ችግር መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ወስዶ ማስቆም እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን:

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አካባቢ፣ ከአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ወጥረትና ግጭት ወደ ከፋ ሁኔታ ሳይሸጋገር መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡ኮሚሽኑ ትናንት ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሥር ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌና ጫሞ 01 የተባሉ አራት ቀበሌዎች፣ ከጋሞ ዞን በመውጣት ልዩ ወረዳ ሆነው ለመደራጀት በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ውዝግቡ እየተባባሰ እንደመጣ አስታውቋል፡፡ኢሰመኮ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ፤ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው እንዲፈቱ ለአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር፣ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ማድረጉን ገልጿል፡

የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለሁለቱም ምክር ቤቶች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጣቸው ምክንያት፣ በጋሞ ዞን አስተዳደር በተለያዩ መንገዶች ሥልታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸመብን ነው በማለት ቅሬታ እንደሚያቀርቡም ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ይሁን እንጂ የዞኑ አስተዳደር የመዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች፣ የአካባቢ ምርጫ ተካሂዶ አካባቢውን ለማስተዳደር ሕግን በተከተለ መንገድ ምርጫውን በማሸነፍ ሥልጣን ሳይረከቡ፣ የአካባቢው መንግሥት ቀበሌዎቹን ማስተዳደር የለበትም በሚል ምክንያት የመንግሥት መዋቅር እንዲፈርስና አካባቢው እንዳይረጋጋ እያደረጉ ነው በማለት ምላሽ መስጠቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ከጥቅምት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችና በጋሞ ዞን አስተዳደር መካከል ባለው አለመግባባት በተፈጠረው ውጥረት፣ ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በኤልጎ ቀበሌ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውል በተፈጸመበት ድብደባ በመሞቱ ምክንያት፣ ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ማምራቱ ተገልጿል፡፡የጋሞ ዞን ፖሊስ አስተዳደር ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ግለሰቡ ከተገደለ በኋላ በተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በነዋሪዎች የሙዝ እርሻዎችና በመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም ከኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ፣ በግለሰቦችና በፀጥታ አካላት በተወሰዱ የኃይል ዕርምጃዎች ለጊዜው ቁጥራቸው በትክክል ባልታወቀ ነዋሪዎችና የፀጥታ አባላት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን፣ በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችና በዞኑ አስተዳደር መካከል በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ አለመግባባቶች፣ በአካባቢው ነዋሪዎችና በፀጥታ ኃይል አባላት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት፣ የዘፈቀደ እስርና የንብረት ውድመት እየተፈጸመ መሆኑን በተመለከተ፣ ክትትልና ምርመራ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ በግለጫው አስረድቷል፡፡በሁለቱ ወገኖች መካከል የቀጠለው ውጥረት፣ ግጭትና እየተወሰዱ ያሉ የኃይል ዕርምጃዎች በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳያስከትሉ ሥጋት እንዳላቸው፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ማስታወቃቸው በመግለጫው ተገልጿል፡፡‹‹የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከዞኑ አስተዳደር፣ እንዲሁም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአፋጣኝ ውጥረቱን የሚያረግብ ሰላማዊ ዕርምጃዎች መውሰድና ዘላቂ መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፤›› ማለታቸውም በመግለጫው ተካቷል፡፡በተጨማሪም ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች መግለጻቸውም ከኮሚሽኑ መግለጫ ጋር ተያይዟል፡፡