ዜና
የትግራይ ክልል ደመወዝ ለመክፈል ያቀረብኩት የአምስት ቢሊዮን ብር ብድር ጥያቄ ምላሽ አላገኘም…

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: January 3, 2024

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያልተከፈለ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችለው የአምስት ቢሊዮን ብር ብድር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የብድር ጥያቄውን ከሦስት ወራት በፊት በደብዳቤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረቡንና አሁንም ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አንድ አመራር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የብድር ጥያቄውን በተመለከተ ሪፖርተር የገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ ነጠሩ የወንድወሰንን በተደጋጋሚ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በ137 ሺሕ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ፣ በፌዴራል መንግሥት በክልሉ የፀደቀው ዓመታዊ በጀት በቂ ባለመሆኑ ጥያቄው መቅረቡን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል የተለያዩ ኃላፊዎችና የመንግሥት ተመራጮች ለሁለት ዓመታት ደመወዝ ባለመከፈሉ በችግር ላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡

በፐብሊክ ፋይናንስ አዋጅ መሠረት የገንዘብ ሚኒስቴርም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር ባይኖርም፣ በአዋጁ መሠረት ግን ብድር መስጠት ይቻላል ብለዋል፡፡

የክልል መንግሥታት ለሚያጋጥማቸው የበጀት እጥረት የፌዴራል መንግሥት ብድር መስጠት እንጂ ቀጥታ ድጋፍ ማድረግ እንደማይችል፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከወራት በፊት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ የጠየቀውን ብድር በሁለት ዓመታት ውስጥ ማለትም በ2018 ዓ.ም. ለመመለስ በማቀድ፣ ጥያቄ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የ2016 ዓ.ም. አጠቃላይ በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 214 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የበጀት ድጋፍ የተያዘ ነው፡፡

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተካተቱበት የክልሎች የበጀት ድጋፍ አመዳደብ ‹ፌዴራል መንግሥት ያለውን የሀብት መጠን፣ የግዴታ ወጪዎችና የበጀት ጫናን ግምት ውስጥ በማስገባት› የተዘጋጀ መሆኑን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል 12.5 ቢሊዮን ብር በጀት የፀደቀለት ቢሆንም፣ ከፌዴራል መንግሥት የሚላከው በጀት ለረጅም ጊዜ ሳይከፈል የቆየውን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል በቂ እንዳልሆነ የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ገልጿል፡፡

‹‹ጥያቄው ከቀረበ ከሦስት ወራት በፊት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ለገንዘብ ሚኒስቴር የበላይ አመራሮች ቀርቦት በመታየት ላይ ነው፤›› ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት አመራር ገልጸዋል፡፡