ዜና
ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻና ወደብ ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነትና የፈጠረው ውዝግብ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: January 3, 2024

ኢትዮጵያ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል የባህር መዳረሻና አስተማማኝ የንግድ ወደብ አገልግሎት ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደስታን ሲጭር፣ በሶማሊያ ፈዴራላዊ መንግሥት በኩል ደግሞ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

ሁለቱ ወገኖች የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን የሚገልጽ መረጃ ሰኞ ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይፋ መደረጉን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያን በተደበላለቀ የመገረምና የደስታ ስሜት ሲገልጹት ተስተውለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተመልካች መሆን እንደሌለባት፣ ኢትዮጵያ በማንኛውም ሰላማዊ አማራጭ መንገድ የባህር መዳረሻ ልታገኝ እንደሚገባ፣ ይህንንም ፍላጎቷን እርሳቸው የሚመሩት መንግሥት እንደሚጀምረውና ቀጣዩ ትውልድ ሊያሳካው እንደሚችል ከጥቂት ወራቶች በፊት ገልጸው የነበረ መሆኑና ይህ ትልም በቅጽበት አንድ ዕርምጃ መጓዙ ትንሽ የማይባሉ ኢትዮጵያውያንን የመገረምና የግራ መገባት ስሜት ውስጥ ከቷቸው ተስተውሏል። የዜናውን መሰማት ተከትሎ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ነዋሪዎች ደስታቸውን በአደባባይና በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻና ወደብ ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነትና የፈጠረው ውዝግብ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ፕሬዚዳንት ሀሰን
ሼክ መሐመድ

‹‹ኢትዮጵያ ካሏት ዋና ዋና ስብራቶች መካከል አንዱ የሆነው ቀይ ባህርን የመጠቀምና የማልማት ፍላጎት መንገድ የሚከፍት የትብብር መግባቢያ ስምምነት ዛሬ ከሶማሊላንድ ወንድሞቻችን ጋር ተፈራርመናል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቴሌቪዥን በተላለፈው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በቀጣይ ዝርዝር ወይይቶችና ስምምነቶች እንደሚኖሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኛ ያሉንን ሀብቶች የመጋራት፣ የመካፈልና በጋራ የመልማት ፍላጎት እንጂ፣ ማንንም በኃይል የማስገደድ ፍላጎት የለንም ስንል የነበረው ሐሳብ ዛሬ በተግባር የምናበስረው የምሥራች ይሆናል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል።

የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በትብብር ለመልማትና ለማደግ እንዲሁም፣ ሁለቱም የጋራ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸው መነሻ ሰነድ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ ዋና ዋና ይዘቶችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ ‹‹ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ካምፕ የምታቋቁምበት የባህር መዳረሻ በሊዝ ለመስጠት ፈቅዳለች። የበርበራ ወደብን ደግሞ ኢትዮጵያ ለንግድ አገልግሎት በስፋት እንድትጠቀምና መሠረተ ልማቶችን እንድታለማ ተስማምታለች፤›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ብሎ ባሰቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ለሶማሊላንድ ድርሻ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለምታገኘው ወታደራዊ ካምፕ ‹‹የምትከፍለው የ50 ዓመት የሊዝ ክፍያ መጠን ምን ያህል ነው?›› የሚለውና ሶማሊላንድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም በኢትዮ ቴሌኮም የሚኖራት ድርሻ በቀጣይ በሚካሄድ ዝርዝር ውይይት እንደሚወሰንም ተናግረዋል።

የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሄ አብዲ በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ‹‹የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ መንግሥትና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። በስምምነቱ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ በይፋ እውቅና የምትሰጥ ሲሆን ሶማሊላንድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ለባህር ኃይል አገልግሎትና ለንግድ አገልግሎት የሚውል ባህር መዳረሻ ለ50 ዓመታት በሊዝ ሰጥታለች፤›› ሲሉ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ኤምባሲ ምክትል ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት ባርካድ ካሪዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፕሬዚዳንቱ የተገለጸውን የስምምነት ነጥብ አረጋግጠው፣ ኢትዮጵያ ለወታደራዊ አገልግሎት የምትጠቀምበት 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የባህር መዳረሻ በሊዝ ለመስጠት ሶማሊላንድ መስማማቷን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለንግድ አገልግሎት የበርበራ ወደብን በስፋት እንድትጠቀም በስምምነቱ መካተቱንና ኢትዮጵያም ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷን ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በሰጡት ማብራሪያ፣ መሠረታዊ የስምምነት ማዕቀፉ የተቀመጠ በመሆኑ፣ በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮቹን በመነጋገር ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ እንደሚሠራ፣ ይህንንም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። ጊዜ የሚጠይቁ ጉዳዮች ካጋጠሙ ደግሞ በሒደት እንደሚታይ፣ ዝርዝር ስምምነቱ ሲጠናቀቅም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ አስረድተዋል።

በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ይፋ ዕውቅና እንደምትሰጥ የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንትና ሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቢገልጹም፣ አምባሳደር ሬድዋንም ሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግን ይህንን አልገለጹም።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ፣ ስምምነቱ ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችለው፣ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ስለሰጠች ብቻ ሳይሆን ሶማሊላንድ እንደ አገር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት ስትችል መሆኑን ይገልጻሉ።

‹‹ይህ ካልሆነ ተፈጻሚነቱ አጠያያቂ ነው›› የሚሉት እኚሁ ባለሙያ፣ ‹‹የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ዝርዝር ስምምነቱ ሲጠናቀቅ ለፓርላማ ቀርቦ የሚጸድቅ ይሆናል ሲሉ ሰምቻለሁ። ሶማሊላንድ ዕውቅና ሳታገኝ ከማን ጋር ተስማማን ብሎ ነው መንግሥት ፓርላማው እንዲያጸድቅለት የሚጠይቀው? ፓርላማውስ በየትኛው ሕግና ምን ብሎ ስምምነቱን ያጸድቀዋል?›› ሲሉ ጠይቀዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሳታገኝ ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርና በመካከል ሶማሊላንድ ስምምነቱን ብታፈርስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይል ከመጠቀም ባለፈ ስምምነቱ እንዲፈጸም የሚያስገድድበት የሕግ ማዕቀፍ እንደማይኖረው አስረድተዋል።

በልላ በኩል የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣን አሰምቷል።

የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሀሰን ሼክ መሐመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሉዓላዊነታችንና የግዛት አንድነትን በመጣስ የፈጸመችውን ሕገወጥ ስምምነት እንደ መንግሥት አውግዘናል፣ ውድቅ አድርገናል። የሶማሊያ ግዛት አንድ ኢንችም ቢሆን በማንም ሊወሰድ አይችልም፣ ሶማሊያ የሶማሊያ ሕዝብ ነች። ይህ የመጨረሻው ነው፤›› ብለዋል።

ማክሰኞ ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን፣ ስብሰባውንም የመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲባሬ መሆናቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም፣ የሶማሌ የምድርና የባህር ግዛት እንዲሁም የአየር ክልሏ በማንኛውም ኃይል እንደማይጣስ አስታውቀዋል።

ካቢኔው ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይም፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ ተግባር ፈጽማለች በማለት ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል።

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ (የሶማሌ ሰሜን ክልሎች) ጋር ያልተፈቀደ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የፈጸመችውን የጥሰት ድርጊት የሶማሊያ መንግሥት በጥብቅ እንደሚያወግዝና እንደማይቀበለው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። መግለጫው አክሎም፣ ሶማሊላንድ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ዋና አካል ሆና ከሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ቀዳሚ ፈቃድና ተሳትፎ ውጭ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማድረግ እንደማትችል አስታውቋል።

የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የእስልምና ትብብር ድርጅት፣ የዓረብ ሊግ፣ ኢጋድና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ለቀጣናውና ለዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲከበሩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የተጠየቀ ሲሆን፣ እነዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት የተመሠረቱበትንና የተቋቋሙበትን ኃላፊነት የሶማሊያ የግዛት ወሰኗን የማስጠበቅ መብቷን በመደገፍና ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች እንድትመለስ ጫና በማሳደር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል። 

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የፈጸመችውን ጥሰትና ጣልቃ ገብነት ለመፍታትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትና የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ስብሰባዎች እንዲጠሩ የሶማሊያ መንግሥት ጠይቋል።

የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ መግለጫ በማጠቃለያው መሠረት፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ጥሰቶችን ለመከላከል ተገቢውን መመሪያ እንደሚያወጣ፣ ለሚወጣው መመሪያ ተግባራዊነትም ሁሉም የአገሪቱ ሕዝብና የመንግሥት ተቋማት ዝግጁ እንዲሆኑ አዟል።

በኢትዮጵያ የሶማሊያ ኤምባሲ አምባሳደርም ወደ አገር እንዲመለሱ ማዘዙ ታውቋል።

ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. ሜይ 18 ቀን 1991 ከሶማሊያ በመገንጠል ነፃነቷን ያወጀች ሲሆን፣ ከ1991 ጀምሮም ራሷን እንደቻለች ገለልተኛና ሉዓላዊ አገር፣ በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥታዊ ሥርዓት ተክላ፣ የራሷ መገበያያ ገንዘብ አትማ በሚታወቅ ግዛት ላይ ውጤታማ የሆነ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ትገኛለች።