

ኪንና ባህል ከለንደን አዲስ አበባ ቅዳሜ የሚገቡት የመቅደላ ቅርሶች
ቀን: January 3, 2024
በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1860 ዓ.ም. ከመቅደላ የተዘረፉ የተለያዩ ቅርሶች ቅዳሜ ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ ተንቀሳቃሽ ቅርሶቹ ከአራት ወራት በፊት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተረከባቸውና በክብር ያስቀመጣቸው ናቸው፡፡
ባለፈው መስከረም ወር ለንደን በሚገኘው ዝነኛው የአቴናየም ክለብ ኤምባሲው ከተረከባቸው መካከል ከብር የተሠሩና በነሐስ የተለበጡ ሦስት ዋንጫዎች፣ በዘመኑ በጦርነት ላይ የዋሉ የጦር ጋሻ ይገኙበታል፡፡

የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የፀጉር ዘለላ በኒውዚላንዳውያን እጅ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሰዎቹ ወደ ለንደን መጥተው አስረክበዋል፡፡
ከመቅደላ አምባ የተወሰደው የመድኃኔዓለም ታቦትን የተረከበችው በለንደን የምትገኘዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ቅርሶቹ ቬሄራዜድ ተብሎ በሚታወቀው የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካይነት ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት የተመለሱ ናቸው፡፡
ቅርሶቹ ቅዳሜ ታኅሣሥ 27 ቀን ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ከደረሱ በኋላ፣ ከ2፡00 ሰዓት ጀምሮ በቅርስ ባለሥልጣን (ሙዚየም) በሚኖረው ሥነ ሥርዓት ርክክብ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የማስመለሱ ጥረት
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሼሄራዜድ ጋር በመተባበር ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ የተለያዩ ቅርሶችን ማስመለሱ ይታወቃል፡፡
መቅደላ ላይ በተሰዉት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከተለያዩ አካባቢዎች ባሰባሰቧቸው ቅርሶች ያደራጁት ቤተመዘክር ዋነኛው የዝርፊያው ሰለባ ነበር።
በመቅደላ ጦርነት በጄነራል ናፒየር ወታደሮች ተዘርፈው ከ250 በላይ በሆኑ ዝሆኖች ተጭነው የተወሰዱት በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ታሪካዊ ቅርሶችና ታቦታቱን ጨምሮ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት በተለያዩ የእንግሊዝ ሙዚየሞችና አብያተ መጻሕፍት፣ እንዲሁም በግለሰቦች እጅ ይገኛሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት ከተመለሱት ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ከሙዚየሞች ሳይሆን፣ በግለሰቦች እጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡት ለጨረታ ለሽያጭ በቀረቡበት አጋጣሚ እንዳይሸጡ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት የተገኙ ናቸው፡፡
በወቅቱ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፣ በመቅደላ ጦርነት ጊዜ ተዘርፈው በእንግሊዝ በአንድ ወታደር ቤተሰብ ይዞታ ሥርና በቤልጂየም የቅርስ ሻጮች እጅ የነበሩ አሥራ ሦስት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ከ154 ዓመታት በኋላ ተረክቧል፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት ከመቅደላ አምባ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው ከነበሩት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መካከል አሥራ ሦስቱን በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተረከበው ጳጉሜን 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡
ኤምባሲው በወቅቱ እንዳስታወቀው፣ የተረከባቸው ቅርሶች የብራና መጽሐፍ ከነማህደሩ፣ ልዩ ልዩ መስቀሎች፣ በነሐስ የተለበጠ የንጉሠ ነገሥቱ የጦር ጋሻ፣ ጽዋ፣ የጳጳስ አክሊል፣ የቀንድ ዋንጫዎች ከወራት በፊት ለሽያጭ ቀርበው የነበሩ ናቸው፡፡ ቅርሶቹን ገዝቶ ለኤምባሲው ያስረከበው ደግሞ ሼሄራዛድ ፋውንዴሽን ነው፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን መስዋዕትነት ተከትሎ በ1860 ዓ.ም. ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች፣ በተለይ ከ500 በላይ የጽሑፍ ቅርሶች፣ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች፣ የንጉሣውያን የወርቅ ዘውዶችና ጌጣ ጌጦች፣ እንዲሁም አሥር የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ታቦታት በእንግሊዝ የተለያዩ ሙዚየሞች ከመገኘታቸውም በተጨማሪም በርካታ ቅርሶች በግለሰብ እጅ እንደሚገኙ ይታወቃል።
‹‹የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ›› በሚል መጣጥፍ ያዘጋጁት ግርማ ኪዳኔ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡
በሦስት ቡድኖች ከተደራጁት ዘራፊዎች ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር እንደነበር ፀሐፊው እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡
‹‹ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቡአቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፉዋቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፤ አልባሳትንም ሸካክተዋል፡፡››
የተዘረፉትን ውድ ቅርሶች ለማስመለስ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በተለይ ከአፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመን ጀምሮ፣ ባለፉት መንግሥታት ከተደረጉት ጥረቶች ባሻገር፣ ‹‹አፍሮሜት›› የሚባለው የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ተቋም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ጥቂት ቅርሶች መመለሳቸው ይታወቃል፡፡ ሦስተኛው ሚሌኒየም ዋዜማ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመቅደላ አምባ ቅርሶች እንዲመለሱ ለእንግሊዝ መንግሥት በደብዳቤ መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡