
ልናገር የአስተሳሰባችን ጥበት ለግለሰባዊና ለአገራዊ ውድቀት እየዳረገን ነው
ቀን: January 3, 2024
በመዝገበቃል አየለ ገላጋይ
አሁን ላለንበት ከእያንዳንዳችን ግለሰባዊ የሕይወት ምስቅልቅሎሽ ባሻገር ያለው አገራዊ ደዌያችን፣ በዚህ ጊዜ ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ የተለያዩ በርካታ ተጨማሪ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችሉም፣ የእያንዳንዳችን ግለሰባዊ የሐሳብ ልዕልና፣ ከአስተሳሰብ ትቢያ ላይ ተፈጥፍጦ መውደቁ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ።
ታዲያ ለእንደዚህ ያለ አገራዊ የህልውና ጥመትና የሐሳብ ልዕልና ድቀት የዳረጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ብዬ ሳስብ በዋና ምክንያትነት ወደ አዕምሮዬ የሚመጡት የሚከተሉት ምክንያቶች ናቸው።
- ጽንፍ የለሽ ድንቁርናችን
እንደ ሕዝብ ደንቁረናል። “ሕመምን ቢሸሽጉት ሬሳ ያጋልጣል” እንደሚባለው ተወደደም ተጠላም ወደ ከፋው ሙታንነት ከመቀየራችን በፊት ይኼን ማመን አለብን። በምናደርገው ድርጊታችን እየተገለጠ የሚታየውን ይኼን ሕዝባዊ የድንቁርና አዚማችንን ማመን አንደኛውና ዋናው የትንሳዔያችን ጅማሬ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ንቃተ ህሊናችንን የተሰለብንና የደነቆርን ትውልዶች ሆነናል። ጥቁር ሰሌዳ ቢገጨንም ጠመኔ ቢቦንብንም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ግን አልታደልንም። እጅግ በጣም ጥቂቶች ሁሉንም ሳላጠቃልል፡፡
ምናልባት በተለያዩ ኮሌጆች ወይም ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማር የትምህርት ሒደት ውስጥ በማለፍ ወይም በመቆየት የተለያዩ ዲግሪዎችን ሰብስበን ይዘን ወጥተን ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን እነዚህ የተለያዩ የትምህርት ደረጃዎቻችንን የሚገልጹ የምስክር ወረቀቶቻችን አሁን ካለንበት አገራዊ ችግር ሊያወጡን አልቻሉም። እንዲያውም በሕይወታችን ያስተናገድናቸውን የጊዜ ኪሳራዎች የሚያሳብቁ ሰነዶች መስለው ይታዩኛል።
የተለያዩ አመለካከቶቻችንን፣ ባህሎቻችንን፣ የሕይወት ተሞክሮዎቻችንን፣ አስተሳሰቦቻችንንና ሐሳቦቻችንን አጣጥመን እንደ አገር ሕዝባዊ አንድነት ለመፍጠርም እያገዙን አይደለም። እንዲያውም ከበረከቱብን አገራዊ የህልውናችን መከራዎች ላይ ራሳችን በራሳችን ላይ ተጨማሪ ችግሮች እንድንሆን ነው ያደረጉን። መማራችን አስተሳሰባችንን በቀናነት ሊያርቀው አልቻለም።
ሁልጊዜም እኔ ነኝ ትክክል ከማለት በስተቀር የሌሎችን የተለየ ንፃሬ ዓለም ባንቀበልም፣ እንኳን የማክበር ይትበሀላችን አናሳ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል። የራሳችንን ሐሳብ ብቻ ከሌሎች ሐሳብ በላይ አድርገን በማሰብ አስገድደን ለመጫን ጥረት እናደርጋለን። እንግዲህ ይኼ ድርጊታችን የሕዝባዊ አስተሳሰብ ጥበታችን አንዱ መገለጫ እንደሆነ ይሰማኛል።
- በአገራዊ ፍርኃት ተወጥረን መያዛችንና አስተማማኝ የደኅንነት ስሜት እያጣን መምጣታችን
አሁን ባለንበት ነባራዊ፣ አገራዊ ሁኔታ ሁላችንም እንደ ግለሰብ ግለሰባዊ ደኅንነታችን በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው ማለት አንችልም። በሥጋትና በፍርኃት ላይ የተመሠረተ ሕይወት ነው እየገፋን ያለነው። ይኼ ደግሞ የውስጥ ሰላማችንን በመንጠቅ ለቅቡፀ ተስፋነት እያጋለጠን ያለ በመሆኑ፣ ነገሮችን አስፍተን የምንመለከትበትን ሕዝባዊ ዓይን ነጥቆናል። አመለካከታችንን ሰፋ በማድረግ የአስተሳሰብ አቅማችንን በማሳደግ አማራጭ ሐሳቦችን ከመጋራት ይልቅ፣ ማጥላላት የተለመደ የሕዝባዊ መገለጫ ይትበሀላችን እየሆነ መጥቷል።
- ከሆነ የታሪክ ስብራታችን በኋላ የተከሰተው የአስተዳደጋችን ብልሹነት
ዘመናዊ መስመር እየተከተለ ያለ የሚመስለን ማኅበራዊ መስተጋብራችን በተለይ በከተማ ቀመሱ የማኅበረሰብ ክፍል የቀደምት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን የሥነ ምግባር እሴቶች እየገፋ በመተው ምክንያት፣ አገር እንደ አገር ትውልድም እንደ ትውልድ የተገነባባቸው እሴቶቻችን ከመዳፋችን ላይ አሙለጭልጨው ወድቀውብናል። ሰውነትን አሽቀንጥረን ጥለን ከእኔነት ማሳ ላይ ብቻ በመብቀል በእኔነት ብቻ ገዝፈናል። እኛነት አይጎበኘንም፣ የእኛነት አጀንዳም የለንም።
በመሆኑም ዕድገቱ በዚህ መንፈስ እየተቃኘ የመጣው ትውልዳችን፣ ሻግተው በበሰበሱ የሐሰት ትርክቶች እየሰከረ አዕምሮው በጥላቻ ተበክሏል። ጥላቻን ብቻ እየጋትን ያሳደግነው ትውልድ ሰዋዊ በሆነ ስሜት ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያውያትን ከመውደድ ይልቅ በቂምና በበቀል ሰክሮ በሠፈርተኛ አስተሳሰብ ሰብዕናው መመረዙ የጠባብ አስተሳሰብ ሰለባ እንዲሆን አድርገን ስላሳደግነው በመሆኑ ውጤቱ አገራዊ የመከራ አዝመራ እንድናጭድ እያደረገን ነው።
- አቅዶ የማጥፋትና የማጣፋት አባዜ
ይኼ በብዛት እየተተገበረ ያለው በ”ኢሊት” ተብየው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ነው። የራሱን ፍላጎትና የሕይወት ሸቅል ተግባራዊና ውጤታማ ለማድረግ፣ ባለማስተዋል በመንጋነት የሚከተለውን የኅብረተሰብ ክፍል ጭዳ አድርጎ ለመስዋዕትነት በማቅረብ እንደ መወጣጫ መሰላል ለመጠቀም ታቅዶ በሚሴር የሴራ ድርጊት የሚሰማራ ቡድን ነው ይኼ ቡድን።
በጠበበ አስተሳሰብ ትውልድን የግል ፍላጎት ማሳኪያ መሣሪያ በማድረግ የግል ጥቅሙን ከማስጠበቅ በስተቀር፣ ሰፊው ማኅበረሰባዊ ኪሳራ ስሜቱን የማይጎረብጠውና ህሊናው የማይሞግተው ጠባቡና ግለኛው ቡድን ልንለውም እንችላለን።
አሁን በትውልዳችን ላይ ሆን ተብለው የሚነዙት የሐሰት መረጃዎችና ትውልዳችንን ወደ ጥላቻ መስመር እየወሰዱት ያሉት የሐሰት ትርክቶች ምናባዊ የታሪክ ፈጠራ ሒደትን በመመርኮዝ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ሆን ተብለው የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት ሲባል ታስቦበት በታቀደ ሴራ፣ በእነዚህና መሰል ቡድኖች ተፈጻሚ እየሆኑ ያሉ ሲሆኑ ትውልዳችንን በሥልት ወደ ተሳሳተ የአስተሳሰብ አቅጣጫ በመምራት አመለካከቱ ተኮድኩዶ የታሰረና የጠበበ ደመ ነፍሳዊ ትውልድ እንዲሆን አድርገውታል።
እኛም ከንቃተ ህሊናችን ማዘቅዘቅ የተነሳ እነዚህን ሆን ተብለው በሆኑ የተወሰኑ አካላት የተፈበረኩ የሐሰት ትርክቶችን ተቀብለን ዕውቅና ስለሰጠናቸውና ነገሮችን አሁን ካሉበት ሁኔታ አንፃር ተመልክተን ትክክለኛ ትርጓሜያቸውን ከመስጠት ይልቅ፣ ባረጀና ባፈጀ እምነትና ዕይታ በመተርጎም ገንዘብ ስላደረግናቸው በቀላሉ ዘለን ከማንወጣበት የጠባብ አመለካከት አዘቅት ውስጥ ከተውናል።
- ርኅራኄ አልባ እየሆንን መምጣታችን
ስሜቶቻችን ከሐዘኔታና ከርኅራኄ ፈጽመው እየራቁ መምጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የእነዚህ የሐዘኔታና የርኅራኄ አልባነት ድርጊቶቻችን መገለጫዎች ዓይነታቸው በርካታ ነው።
የሌሎችን ስሜትና ያሉበትን ሁኔታ በእነሱ ጫማ ውስጥ ቆመን ለመገንዘብ ፈቃደኝነቱ ከውስጣችን ተሟጦ አልቋል። ራስ ወዳድነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈ ስለሄደ የርኅራኄ መንፈሳችንን አሳጥቶ ውጦናል። ራስ ወዳድነትና ጥቅመኛነት እየጎሉ የመጡ የሕይወት መመርያዎቻችን ሆነዋል። ከአመለካከታችን መጥበብና አናሳነት የተነሳ ርኅራኄ ልባችንን እንዲጎበኘው ፈቃደኞች አይደለንም። ይህንን ማድረግ አይደለም ማሰብ በራሱ ለትውልዳችን እንደ ቋጥኝ ድንጋይ እየከበደው ከመጣ ሰነባበተ።
- ደመነፍሳዊና ምክንያት አልባ ስሜታዊነታችን
አሁን አሁን የብዙዎቻችንን ድርጊቶች ስንታዘብ በምክንያታዊነት ላይ ሳይሆን፣ በስሜታዊነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በመሆኑም የተለያዩ አማራጭ ምልከታዎቻችንን በመቀማት በስሜታዊነት ላይ የተመሠረተና ስህተትን የተጎናፀፈ ውሳኔ እንድንወስን አድርጎናል፣ እያደረገንም ነው። የአስተሳሰባችን ጠባብነት እየተከሰተበት ያለው ሌላው ዘርፍ መሆኑ ነው።
- በምክንያተ ቢስ መንጋዊነት ላይ የተመሠረተው አስተሳሰባችን
በእርግጥ በብዙ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶችን ቢቻል ለማስወገድ ያለበለዚያ ለመቀነስ ሲባል፣ በበርካታ ነገሮች የሚመሳሰሉ አካላት የተለያዩ የአብሮነት ምኅዳሮችን በአብሮነት መመሥረትና ውሳኔዎችን በጋራ ተወያይቶ መወሰን የተለመደና ተገቢ ነገርም ነው። አሁን አሁን እየተመለከትነው ያለው ነገር ግን ነገሮችን በራሳችን አጢነን በመገንዘብና ተገቢነታቸውን በኅሊናዊ ሚዛን በመመዘን ሳይሆን በመንጋዊ ተጎታችነት በደመነፍስ ነው እያከናወንናቸው ያሉት። ይኼ ደግሞ አመለካከታችንንና አስተሳሰባችንን ጠፍንጎ በማሰር የተለያዩ አማራጮችን እንዳናይና አስተሳሰባችን እንዳይሰፋ ያደረገን ሲሆን፣ ከልዩነቶቻችንም ጋር በመከባበር እንዳንስማማ አድርጎናል።
- በአስተሳሰብ ጠባብነት ላይ የተመሠረቱት ግለሰባዊ ባህሪዎቻችን
ተዘውትረው የሚንፀባረቁት ግላዊ ባህሪዎቻችን በመጣንባቸው የሕይወት መስመሮች ሻካራነትና ለስላሳነት ላይ ተመሥርተው የተሠሩ ናቸው። እንዲሁ በድንገት ከመሬት ተነስተው የተፈጠሩ አይደሉም። ግትርነት፣ እልኸኝነት፣ ቁጡነት፣ ትዕግሥት አልባነት፣ ወዘተ የመሳሰሉት አሉታዊ ግላዊ የሆኑ ባህሪያት ለአስተሳሰብ ጥበት የሚያበረክቱት አሉታዊ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም።
በመሆኑም እነዚህ አሉታዊ ባህሪዎቻችን በማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ላይም ሆነ በግላዊ ሕይወታችን ላይ የተለያዩ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን ታሳቢ በማድረግ ሥራዎቻችንን እንዳናከናውን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም እንደ አገር አሉታዊ በሆነ መንገድ አቅማችንን እየመጠጡ ለአስተሳሰብ ጠባብነት ዳርገውናል ብል እያጋነንኩ አይመስለኝም።
በመጨረሻም በተለያዩ ዓውዳዊ የሕይወት ክዋኔዎቻችን ላይ እየተንፀባረቁ ብሔራዊ መደማመጣችንን ነጥቀው ቋንቋችንን የከለዳውያን ያደረጉብንን ጠባብ አመለካከቶቻችንን ከሕይወታችን ፍቀን ለማስወገድ የልብ ፈቃደኝነትን፣ አስተዋይ ንቃተ ኅሊናን፣ የአስተሳሰብ ግልጽነትን፣ ራሳችንን የምናውቅበትንና በኋላ ቀርነት ከሚፈትናቸው ጎጂ እምነቶች ነፃ የምንወጣበትን ጥበብ ራሱ ጥበብ የሆነ የጥበብ ምንጭ እግዚአብሔር እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብና እንደ አገር ያድለን እላለሁ።
አመሠግናለሁ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡