
ልናገርሕዝብን በትምህርትና በልማት ያላራመደ መንግሥት የሚወሳበት ታሪክ አይኖረውም
በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስነገሬን “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” በተሰኘ በሚከተለው ኢትዮጵያዊ ተረት እጀምራለሁ። አንድ ፍልፈል ልጅ ይወልዳል፣ የወለደው ልጅም ከእሱ በመልክ የሚሻል የደም ግባት ያለው ነበር። በዚህ ምክንያትም አባቱን ይጠላው ጀመር። አባቱ ያለ መሰልቸት ተራራን እየቆፈረ በከፍተኛ ድካም በመኖሩ መጎሳቆሉን ከቶም አልተረዳም።ይኼ ቆንጆ ፍልፈል አንድ ቀን ወደ ሰማይ አንጋጦ ሲመለከት የፀሐይን ውበት ያያል። እናም ወደ አስቀያሚ አባቱ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹አባቴ ሆይ አንተ አስቀያሚና ሻካራ ሰውነት ያለህ ነህ፡፡ አስቀያሚ አባት አልፈልግም። እናም ፀሐይ አባት እንዲሆነኝ ሄጄ ብጠይቀው ቅር ትሰኛለህን?›› ብሎ ጠየቀው። አባትም በጥያቄው ግራ ቢገባም፣ “እሺ ካለህ ሄደህ ጠይቀው” ይለዋል በቅሬታ ድምፀት።
ፍልፈሉም ብር ብሎ ወደ ፀሐይ ይሄድና፣ ‹‹የምታምረው ፀሐይ ሆይ አባት ሁነኝና ከአስቀያሚው አባቴ ገላግለኝ›› ይለዋል። ፀሐይም ‹‹አይ ወጣት መሆን፣ አወይ ከዕውቀት መራቅ የእኔ ውበት እኮ የሚወሰነው በደመና ነው። ደመናው ሲጋርደኝ ውበቴ ይጠፋል። ሥልጣን ያለውን ደመናንን አባት ብታደርገው ይሻልሃል›› ይለዋል። ፍልፈሉም ወደ ደመና ቀርቦ አንተ የፀሐይ የበላይና ውበት ሰጪና ነሺ ስለሆንክ አባት ሁነኝ ሲል ይማፀናል። ደመናም ‹‹ብሆንህ ደስ ባለኝ፣ ነገር ግን እኔም ንፋስ የተሰኘ አለቃ አለብኝ። በአንድ ጊዜ ድምጥማጤን የሚያጠፋ ባለሥልጣን፣ እናም የበላዬ ንፋስ አባት ይሆንህ ዘንድ ሂድና ጠይቀው›› ይለዋል።ፍልፈልም ወደ ንፋስ በመሄድ አባት እንዲሆነው ቢጠይቀው፣ ‹‹የእኔ አለቃ ወይም የሚያሸንፈኝ ተራራ መሆኑንን ታውቃለህን? ካላወቅህ የበላዬ ተራራ የአንተ አባት ብሆን ይቃወመኛልና ወደ ተራራው ሂድና አባት ይሆንህ ዘንድ ጠይቀው…›› ይለዋል።ወጣቱና ቆንጆው ፍልፈል ተመልሶ ምድር ላይ ወዳለው ተራራ ይሄዳል። ከተራራው ጋርም ይገናኛል። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ውጣ ውረዱን ዘርዝሮ፣ ‹‹ንፋስ በአቅሜ እንዳልጠቀም የሚጋርደኝ ተራራ ነው፣ ኃያሉና ቆንጆው ተራራ ነው ስላለኝ ተራራ ሆይ አባት ሁነኝ…›› ይለዋል።ተራራም ይህንን የፍልፈል ታሪክ ሰምቶ ይገረማል። የተገረመውም የፍልፈል ልጅ መሆኑን አውቆ አላዋቂነቱን አስተውሎ ነበር። እናም ለፍልፈሉ፣ ‹‹ወጣቱ ና ውቡ ፍጥረት ሆይ ምንም እንኳ ስምህን ባላውቀውም በልፋትህ አዝኛለሁ። ለመሆኑ እኔ የበላይ እንዳለኝ ታውቃለህን? አታቅም መሰል። ይኸውልህ የእኔ የበላይ ሌት ተቀን ሆዴን እየቦረቦረ የሚንደኝ ፍልፈል ነው። ፍልፈል አባት ይሁንህ…›› አለው በሆዱ እየሳቀ።ወጣቱ ፍልፈልም እየሮጠ ወደ አባቱ ተመልሶ፣ ‹‹አባቴ ሆይ ከሁሉ የሚበልጥ ተራራን የሚንድ ኃይል እንዳለህና በኃይልህም ክብር እንዳገኘህ ባለማወቄ አባት በማማረጥ በከንቱ ደከምኩ። ለካስ ከአንተ የሚበልጥ ጀግና አባት የለም…›› አለ ይባላል፡፡ይህን ተረት በማስቀደም ጽሑፌን የጀመርኩት ተራራን የሚንድ ኃይል፣ ተራራን የሚያርበደብድ ጉልበት እንዳለን በመዘንጋት በምናየው ብልጭልጭ ነገር በመዘናጋት ወይም በሥጋ ምቾት በመጠመድ ገነትን በአገራችን በመፍጠር ልጆቻችን ፈታ ዘና ብለው እንዲኖሩ ከማድረግ ይልቅ፣ የበለፀጉት አገሮች ውጫዊ ውበት እንዲማርካቸውና “ምነው ኢትዮጵያዊ ሆኜ ባልተፈጠርኩ” ብለው እንዲማረሩ፣ እርስ በርስ እየተገዳደልን ከደርግ እስከ ብልፅግና መዝለቃችን እጅግ አስገርሞኝ ነው።እርስ በርስ የሚገዳደሉት የሰው ልጅ በሁለት ተቃራኒ ፆታዎች ግንኙነት እንደተፈጠረ እንኳን አይገነዘቡም። የአይሁድ፣ የክርስትናና የሙስሊም እምነቶችን ቢከተሉም እንኳን እንዳይኖሩበት ንቃተ ህሊናቸው ይገድባቸዋል። በዝቅተኛ ንቃተ ህሊናቸውም ሰበብና በዳቦ ጥያቄ የተነሳ ለከንቱ መስዋዕትነት ይሠለፋሉ።የኢትዮጵያውያን እምነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ሆኖም እምነትን ተገን አድርገው የሚኖሩበት እጅግ ጥቂቶች በመሆናቸው አገራችን ፍቅር፣ ሰላምና ተስፋ አጥታ ልጆቿ በሰቀቀን እየኖሩ ነው። ፈጣሪያቸውን እያማረሩና “ለምን ፈጠርከን!” እያሉም ነው፡፡ሁላችሁም እንደምታውቁት የእምነት ጉዳይ በሎጂክ ማሳመንን ወይም ሳይንሳዊ ግኝትን አይጠይቅም፡፡ እናም ኢትዮጵያውያን አማኞች “ለምን ፈጠርከን!” ብለው ማማረራቸው አያስገርምም።እምነት ፈጣሪህን ሳታየውና መኖሩንም ሳታረጋግጥ ስለመኖሩ፣ ስለኤልሻዳይነቱ፣ ስለሁሉን ፈጣሪነቱና ተቆጣጣሪነቱ… የምትመሰክርለት እውነት ነውና፣ ይህንን እምነት ነው በሃይማኖት የምንለው። እምነት የፈጣሪና የተፈጣሪ ወይም የፍጡራኑ ጉዳይ ነው።ይሁን እንጂ የፍጥረት ጉዳይ የሚያመራምራቸው ፈላስፎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ አሳቢያን፣ እምነተ አልባ ምሁራንና ሳይንቲስቶችም እንዳሉ መካድ አይቻልም። እነዚህ ምሁራንና ሊቃውንት የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረ ከ300,000 ዓመታት በላይ እንደሆነው በምርምራቸው ቢያቀርቡም፣ ዛሬም ቆዳውን የሚያዋድድ ፍጡር መሆኑ በእጅጉ ያስገርማቸዋል። ሎጂክና ሳይንስን አጣምረው፣ “ሰው አንድና ያው” እንደሆነ በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ትንታኔ ቢያቀርቡም፣ ይህንን ተጨባጭ እውነት ባለማወቅ በአፍሪካ ወንድም ወንድሙን በነፃ አውጭነት ስም በመግደል ለዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በቅቷል።ሊቃውንቱ በቅሬታ5 አካል ምርመራቸው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ባሏትና በአርዲና በመሳሰሉት ላይ እንኳን ባካሄዱት ጥናትና የአፅም ምርመራ፣ በዋነኝነት የሰው አፈጣጠር መነሻ ከእነዚህ ሳይሆን አይቀርም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። በሁለት እግሩ ቆሞ የሚሄድ ሰው መሰል ፍጡር ሄሞ ኢሬክተስ ከሦስት ቢሊዮን ዓመታት አስቀድሞ እንደነበር በኢትዮጵያ በአፋር ክልል የተገኘው “የድንቅነሽ ወይም ሉሲ” አፅምም ይመሰክራል በማለት ይሞግታሉ።ሰው ከእነ ሉሲ እናትና አባት በሁለት ተቃራኒ ፆታ ተነስቶ ዛሬ ስምንት ቢሊዮን ድረሰ ወይስ ለእኛ ለሸክላዎቹ ፍጡራን “ፈጣሪያችን ባይገለጽልንም” ከአዳምና ከሔዋን ተነስቶ ዛሬ ስምንት ቢሊዮን ሆነ የሚለውን እኩል ለክርክር ማቅረብ ባይቻልም፣ የሰው መሠረቱ “አንድና ያው” እንደሆነ ልናሰምርበት ይገባል። ዛሬ የሰው ዘር እንደ ምድር አሸዋ በዝቷል። ይህ ዘሩ እንደ ምድር አሸዋ የበዛውን ሰው በደምሳሳው፣ ዝርያህ አንድ ነው ብሎ ማስረዳት ግን ቀላል አይደለም። በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታዎች ተለዋዋጭነትና በአየር ንብረቱ ሰበብ መልኩ ጥቁር፣ ነጭ፣ ወይም ዥንጉርጉር ሊሆን ችሏልና፡፡ ይህ እውነት ግን በዘርፈ ብዙ የዕድገት ችግር ውስጥ ባሉ ታዳጊ አገሮቾ ዘንድ እምብዛም አይታወቅም። ይህ እውነት በስፋት እንዳይታወቅም ከዜጎቻቸው ከጥበብ መራቅ የተነሳ “ሃይ ባይ ባጣ ዘረፋ ላይ የተሰማሩ” ላልተቋረጠ ሥጋዊ ተጠቃሚነት ሲሉ ለዘመናት ዕውቀትን አዳፍነው ነበር። በንቃተ ህሊናቸው ምጥቀት አማካይነት በሠሩት ሀዳይ መሣሪያ አፍሪካን እያስፈራሩና እርስ በርስም እያጫረሱ ይኸው ለዘመነ ግሎበላይዜሽን ደርሰዋል።እንደሚታወቀው ንቃተ ህሊና ሲያድግ የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታ እንደሚቀየር በአንክሮ የበለፀጉ አገሮች፣ ሕዝቦችና የአኗኗር ሁኔታ በመቃኘት ለማወቅ ይቻላል። የበለፀጉ አገሮች የመበልፀጋቸው ምክንያት በአገራቸው ከፍተኛ ዕውቀት ከማፍራቱም በላይ፣ ሕግና ሥርዓት የቆመበት ምሰሶ እጅግ ጠንካራ በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተጓዙበት መንገድ በእንቅፋት የተሞላ እንደነበር ማስታወሱ፣ በአንድ ክፍለ ዘመን ብቻ በትምህርት ዕውቀታቸው በልፅጎ ጥበበኛ ለመሆን እንደቻሉ እንድገነዘብ ያስችለናል።እና ለምንድነው ያልበለፀጉ አገሮች ከጋረዳቸው አላዋቂነት ለመላቀቅ በትምህርት በልፅገው እንዳይለወጡ ተንኮል፣ አሻጥርና ሴራ በመጎንጎን የሚጠመዱት? የበለፀጉ መንግሥታት ከገዛ ጥቅማቸው አንፃር ብቻ ወዳጅነታቸውን በማሥላት፣ የአፍሪካ አገሮች በዕዳ ጫና እየማቀቁ በድህነት ውስጥ እንዲዳክሩ የሚያደርጉት? የአፍሪካ መንግሥታትስ ከበለፀጉ አገሮች መንግሥታት ጋር በመተባበር ሕዝቦች በድንቁርና፣ በጦርነት፣ በረሃብ፣ እንዲሁም በፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለዘመናት እንዲዳክሩ ሲያደርጉ የሚስተዋለው? ለታሪክና ለአገር ተረካቢው ትውልድ እንዴት አያስቡም?የበለፀጉት አገሮች አፍሪካን ለሸቀጥ ማራገፊያነት፣ ለጦር መሣሪያ መለማመጃና መቸብቸቢያነት፣ እንዲሁም በቱጃሮቻቸው ለሚዘወሩ ባንኮቻቸው ለትውልዳቸው ጥሪት ለማስቀመጥ ሲጥሩ የአፍሪካ መንግሥታት ግን አገርን በመዝረፍ፣ በበለፀጉ አገሮች ካዝና ለልጆቻቸው ጥሪት ለማከማቸት ለዘመናት በዘረፋ ተሰማርተው በሴራ እርስ በርስ ዜጎቻቸው እንዲበላላ እያደረጉ በአመፅ ከአገር ሲሰደዱ ለምን ይስተዋላል?ይህ በጥያቄ ላይ ያተኮረ ከላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ሲፍታታ አያሌ ምሥልና ትንተና እንደ አገሮቹ የታሪክ ዓውድ ይሰጣል። በአፈጣጠሯ ሀብታም በሆነችው አፍሪካ በአጠቃላይ የታላላቆቹ አገሮች ሹማምንት ሕልም በሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ ዜጎች እርስ በርሳቸው በመገዳደልና ጥላቻ በመስበክ በድህነት ዕቅፍ ውስጥ እንዲኖሩ የተፈረደባቸው፣ ለብዝበዛና ለዘረፋ እንዲመቹ በመደረጋቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት።ለምን ይመስላችኋል አፍሪካ እንደ አውሮፓውያን ጠንካራ ኅብረት እንዲኖራት ያልተፈለገው? አገሮች ቀጣናዊ የሆነ አብሮ የመበልፀግ ትስስር በማድረግ በአጭር ጊዜ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ሲችሉ፣ ይህም ቀርቶ በተናጠል እንዳያድጉ እንኳ በእያንዳንዱ አገር ሰላም እንዳይሰፍን የበለፀጉ አገሮች ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን በእጅ አዙር ተቆጣጥረው አገሮቹን ለሸቀጣቸው ማራገፊያነትና ለማዕድናት ብዝበዛ ብቻ እየተጠቀሙባቸው ነው። የበለፀጉት አገሮች በእጅ አዙር እያስራቡም የተቀቀለ ስንዴ ይመፀውታሉ።ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎቻቸውንም በብዙ ቢሊዮን ዶላር ያውም በብድር በመሸጥ ተበዳሪ ለአበዳሪው ሳይወድ በግዱ ባርያ እንዲሆን ያደርጉታል፣ በዕዳ ወገቡን አጉብጠው። የሚገርመው ነገር ሰላም የሰፈነበትና ዜጎች በልተው የሚያድሩበት አገር እንዲፈጠር የሚያደርጉት፣ በሚገርም ሁኔታ ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን በተቆጣጠሩበት ደሃ አገር ሀብት ብቻ ነው። ባንኩም፣ የጦር መሣሪያውና ጦሩ፣ እስር ቤቱና አዛዡ እነሱ በሆኑበት አገር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ መግሥትን ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ኢሕአዴግ ብንቃኝ እንኳ ይህንን እውነት እንገነዘባለን።በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተሞከረውን ራስን በኢንዱስትሪ የመቻል ሙከራ እንግሊዞች አጨናግፈዋል። አፄ ሚኒልክ ከፈረንሣይ ጋር ተጣብቀውና ጂቡቲን እስከ ወደቧ በሊዝ ለፈረንሣይ አስረክበው በእጅ አዙር ቅኝ ተገዥነት ሥር ሆነው አገሪቱን በሰላም በመምራታቸው ዘመናዊነትን ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ አስገብተዋል። በዓድዋ በኢጣሊያን ጦር ላይ የተቀዳጁት ድልም ለአፍሪካ ኩራት ሆኗል። ምኒልክ በዲፕሎማሲ የሚታሙ ባይሆንም በሊዝ ለ99 ዓመታት ለፈረንሣይ የተሰጠችው ጂቡቲ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ ኮንትራቱ ቢያበቃም አስታዋሽ አጥቶ ጂቡቲ ራሷን የቻለች አገር ሆናለች።ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ለ44 ዓመታት ኢትዮጵያን መርተዋል። በዚህ ረዥም ዓመት ውስጥ በተገቢው መጠን ለአገር ልማት አልሠሩም። ይህንን እውነት በተጨባጭ ኢኮኖሚስቶቹ አብራርተውታል።የኢትዮጵያን ዕምቅ ሀብት በማልማት የበለፀገች አገር ለማድረግ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ከልማት ይልቅ ለዙፋናቸው ቀጣይነት በእጅጉ ስለተጨነቁ የሕዝቡን የልማትና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ አልቻሉም። እርግጥ ነው ከሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. በኋላ፣ የኢጣሊያ ዳግም ወረራ መስከረም 28 ቀን 1928 ዓ.ም. ተጀምሮ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. መቋጨቱ ይታወቃል፡፡ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቁጭት ለዘመናዊ ትምህርትና ለቴክኖሎጂ ተደራሽነት አበክረው ሠርተዋል። ይሁን እንጂ ከሠሩት የተሻለ እንዳይሠሩ የራሳቸው ንቃተ ህሊና የምሁራንን ምክር እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል። ወደ ደርግ ስንመጣ የሶሻሊዝም ኮሙዩኒስታዊ ግብ መክሸፍና የዓለም የሁለት ጎራ ፖለቲካ ገመድ ጉተታ በታኅሳስ ወር 1983 ዓ.ም. ማክተም እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርጎበት ነበር፣ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ዘመነ ሥልጣኑ ያከተመው። በእኔ ምልከታ ሶሻሊዝም በወቅቱ እንደ ፑቲን ዓይነትና እንደ ዛሬዋ ቻይና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ያለው መንግሥት ቢኖረው ኖሮ አይፈርስም ነበር። የእነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ሕልም አይጨናገፍም ነበር።የሶሻሊዝም ሥርዓት መክሸፍ ሰበቡ የኮሙዩኒዝም ወይም የሶሻሊዝም ሥርዓት መንኮታኮት ነው። ደርግን የተካው ኢሕአዴግም ጠንካራና ደካማ ጎን ነበረው። ጠንካራ ጎኑ የተከሰተው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት በመረዳቱ ነው። ከዚያ በፊት ጨዋታው ሁሉ የዘረኝነት ነበር። ይህ መንገድ እንደማያዋጣና በዓለም ላይ የሌለ ሥርዓት መሆኑን የተረዳው በምርጫ 97 ክርክር ወቅት ነበር። የምርጫውን ድልና በመለስ የተካሄደውን እጅ መቁረጥም ታሪክ መዝግቦታል። ዛሬስ? ስለዛሬው መንግሥት ፈተናና የሕዝብ ሰላም ዕጦት ማውሳት ለቀባሪው ማርዳት በመሆኑ ትቼዋለሁ። የአገሬ ፖለቲከኞች ግን በሞት ኃላፊ እንደሚሆኑ ማወቅ እንዳለባቸው በትህትና አስገነዝባቸዋለሁ። እንደ ማንኛውም ሰው ዛሬ ወይም ነገ ትሞታላችሁ (ነገ ሁሌም ነገ እንደሆነ ግን አትዘንጉ)፡፡ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል የምትሉትን በተጨባጭ ከሠራችሁለትና በዕውቀት የምታበለፅጉት፣ ከረሃብና ከዕርዛት ከገላገላችሁት ነገ በታሪክ ትመሠገናላችሁ። ታሪካችሁም ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል። በእርግጠኝነት ሥራችሁ ለትውልድ ይሸጋገራል። ሕዝብን በትምህርትና በልማት ያላበለፀገ መንግሥት ነገ የሚወሳበት ታሪክ የለውም። ከኮሙዩኒስቷ ሶቭየት ኅብረት መንኮታኮት በኋላ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ያለፉ በጎ ሰዎች ሳይቀሩ ምንም እንዳልሠሩ ሁሉ እንደ ዋዛ ከወርቃማው የታሪክ መዝገብ መፋቃቸውን ዕወቁ።ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው mekonnenshawelsun@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡