
ከ 5 ሰአት በፊት
አሜሪካና ዐሥራ አንድ አጋሮቿ የየመን ሁቲዎችን አስጠነቀቁ።
አሜሪካና አጋሮቿ ሁቲዎችን ያስጠነቀቁት ከእንግዲህ በመርከቦች ላይ የሚደርስ ጥቃት ካለ የአጸፋ ምላሹ የዋዛ እንደማይሆን በማስገንዘብ ነው።
አሜሪካና ዩኬን ጨምሮ ሌሎች ዐሥር አገራትን ያካተተው ጥምር ኃይል በቀይ ባሕር ደኅንነትን ለማስጠበቅ እየተጋ እንደሆነ ይታወቃል።
ይህ ጥምር ኃይል የሁቲ አማጺያን በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል ቢሞክርም ሁቲዎች ግን ጥቃታቸው ጋብ አለ እንጂ አልቆመም።
ይህ ያሳሰበው ጥምር ኃይሉ የመጨረሻ ያለውን ማሳሰቢያ ለሁቲዎች ልኳል።
ሁቲዎች ከኅዳር ወር ጀምሮ በትንሹ 20 ጥቃቶችን በቀይ ባሕር እያለፉ በነበሩ የንግድ መርከቦች ላይ ፈጽመዋል።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ለሐማስ ያላቸውን የማያወላዳ ድጋፍ ከገለጹ ሰነባብተዋል።
ሁቲዎች እንደሚሉት ጥቃት እያደረሱ ያሉት በሁሉም የንግድ መርከቦች ሳይሆን ከእስራኤል ጋ በሚገናኙት ላይ ብቻ ነው።
እስራኤልና አጋሮቿ ግን ይህ መረጃ ሐሰት ነው ይላሉ።
የአሜሪካና የዩኬ ባሕር ኃይሎች የተወሰኑ የሁቲ ሚሳኤሎችን መምታት ችለዋል። ጀልባዎችንም አቃጥለዋል። የሁቲ አማጺያንን ገድለዋል።
ይሁንና ከዚህ ቀደም በቀጥታ ወደ የመን ጥቃት አድርሰው አያውቁም።
ከእንግዲህ ግን ምናልባት በሁቲ ጥቅሞች ላይ እንዲሁም ወታደራዊ ቀጠናዎች ላይ ቀጥተኛ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ነው ጥምረቱ ያስጠነቀቀው።
ይህ አሜሪካ መራሹ የሆነውና የቀይ ባሕር ዘብ እሆናለሁ ያለው ጥምር ኃይል ዩኬ፣ ካናዳ፣ ባሕሬን፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ እና ኒውዚላንድን ያካተተ ነው።
ጥምሩ ባወጣው መግለጫ በቀይ ባሕር የሁቲ ጥቃቶች ‘ሕገወጥ፣ ተቀባይነት የሌላቸውና አዋኪ’ ሲል ጠርቷቸዋል።
ከዚህ በኋላ ሁቲዎች ለሚሰነዝሩት ጥቀት ይህ ቡድን ቀጥታ ወደ የመን ያነጣጠረ አጸፋ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።
ምናልባትም የአሜሪካ መራሹ ጥቃት በሁቲ የሚሳኤል ማከማቻ ላይ ያነጣጠረ ይሆናል።
የዓለም 15 ከመቶ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ በቀይ ባሕር በኩል ነው።
የሁቲዎችን ጥቃት ተከትሎ የመርከቦች ጉዞ የተስተጓጎለ ሲሆን ይህም የዓለም የገበያ ሰንሰለትን አውኮታል።
የነዳጅ ዋጋ ሊያሻቅብ ይችላል የሚሉ ስጋቶችም ከወዲሁ አሳሳቢ ሆነዋል።
- “በዚህ ስምምነት የሚጎዳ ማንም ሃገር የለም፤ ሕግም አልተጣሰም” የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት3 ጥር 2024
- በአፍሪካ ዋንጫ እና በእስያ ዋንጫ ምክንያት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚያጧቸው ተጫዋቾቸ የትኞቹ ናቸው?ከ 6 ሰአት በፊት
- በኢራን ቃሲም ሱሌማኒ መቃብር አካባቢ በፈነዳ ቦምብ ቢያንስ የ103 ሰዎች ህይወት አለፈ3 ጥር 2024
የዓለም የንግድ መርከብ ኅብረት ባወጣው መረጃ 20% የዓለም የንግድ መርከቦች ቀይ ባሕርን እንደመሸጋገሪያ መጠቀም ማቆማቸውን ይፋ አድርጓል።
ይህም የሆነው የሁቲን ጥቃት በመስጋት ነው።
መርከቦቹ ቀይ ባሕር አካባቢ ሰላም ባለመሆኑ በደቡብ አፍሪካ ዳርቻ በኩል ዙርያ ጥምጥም ጉዞን ለማድረግ ተገደዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የዕቃ መዘግየትን እያስከተለ ነው።
አሜሪካ ሁቲ ለሚፈጽማቸው ጥቃቶች ዋንኛዋ ተጠያቂ ኢራን እንደሆነች ትገልጻለች።
ኢራን በበኩሏ እጄ የለበትም ስትል ታስተባብላለች።
ሁቲዎች በዋናነት በባብ አል መንደብ ሰርጥ የሚያልፉ መርከቦችን ዒላማ ታደርጋለች። ባብ አል መንደብ በኢሲያና አፍሪካ መሀል ጂቡቲን የመንን እና ኤርትራን የሚነካ የ32 ኪሎ ሜትር የባሕር ክፋይ ነው።
ሁቲ በየመን አናሳ ቁጥር ባላቸው ዛይዲስ በሚባሉ የሺአ ሙስሊሞች የሚመራ የፖለቲካ ኃይል ነው።
ሁቲ የሚለውን ስም የዛይዲ ሺአ ተከታይ በሆነውና የሁቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴውን ከመሠረተው ሁሴን አል ሁቲ ስም የተወሰደ ነው።
የሁቲ አማጺያን ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ከየመን መንግሥት ጋር ጦርነት የገጠሙ ሲሆን ኋላ ላይ በየመን የተነሳውን አመጽ ተከትሎ ዋና ከተማዋን ሰነአን እንዲሁም ሰሜናዊ የመንን እና ቀይ ባሕር ጠረፍን መቆጣጠር ችለዋል።
ከሁቲዎች በተቃራኒ ያለውን መንግሥት ሳኡዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ይደግፉታል።