በጄፍሪ ኤፕስቲን
የምስሉ መግለጫ,በጄፍሪ ኤፕስቲን

ከ 1 ሰአት በፊት

የወሲብ ቅሌት ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ፍርድ ቤት አዳዲስ ሰነዶችን ይፋ ተደርገዋል።

በነዚህ አዳዲስ ሰነዶች ከተጠቀሱ ታዋቂ ሰዎች መሀል ልዑል አንድሪው ናቸው።

ዳኛው መዝገቦቹ እንዲለቀቁ ከኤፕስቲይን ተባባሪ ጂሌይን ማክስዌል ጋር በተገናኘ የህግ ጉዳይ አካል ሆኖ ትእዛዝ ሰጥቷል።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ቢል ክሊንተን እና ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ሰነዶቹ ስማቸው የተጠቀሰ ቢሆንም አንዳቸውም አልተከሰሱም።

በ2019 የሞተው ጄፍሪ ኤፕስቲን ከወሲብ ንግድ ጋር በተያያዘ በርካታ ስሞች ይፋ መደረግ ጀምረዋል።

ብዙ አነጋጋሪ የሆነውና 900 ገጾች ያሉት ዶሴ ብዙ አዳዲስ ስሞች በቅሌት ይገለጡበታል ተብሎ ቢጠበቅም ያ አልሆነም።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ሰነዶች በመጪዎቹ ቀናት ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስማቸው ከተጠቀሰ ከ100 በላይ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በስህተት የተከሰሱ ሲሆን ሌሎች በፍርድ ቤት መዝገቦች ላይ ውንጀላ እያቀረቡ ነው ወይም ምስክሮች ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።

ሰነዶቹ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ልጆችን ሴተኛ አዳሪ አድርጎ ለወሲብ ንግድ በመጠቀም ጥፋተኛ ተብሎ ፍርድ ሲከታተል በነበረው ኤፕስቲን ዙርያ ያሉ ሰዎችን ስም ያወጣል ተብሎ ይገመታል።

የኒውዮርክ ዳኛ ሎሬታ ፕሬስካ ፋይሎቹ እንዲለቀቁ ትእዛዝ ሲሰጡ፤ ብዙዎቹ ስሞች ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙሃን መገለጻቸውን አስታውሰዋል።

ሌሎች በርካቶች የሰነዶቹን መውጣት ተቃውሞ አላነሱም ብለዋል። ዳኛ ፕሬስካ የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን ለመከላከል አንዳንድ ስሞች እንዲቀየሩ ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ፋይሎቹ እ.ኤ.አ. በ 2001 ልዑል አንድሪው በኤፕስቲን ማንሃተን አፓርታማ ውስጥ “ሶፋ ላይ ተቀምጠው ጡቴን ነካክተዋል” ስትል የተናገረችው የጆሃና ዮበርግን ቃል ዋቢ አድርገዋል።

ቤኪንግሃም ቤተመንግሥት ይህንን ክስ መሠረተ ቢስ ሲል ውድቅ አድርጎታል።

ቀደም ሲል በተጠቀሰ አንድ መግለጫ ላይ፤ ዮበርግ በሰጡት ቃል ልዑል አንድሪው ከሌላ ከሳሽ ቨርጂኒያ ጄፍሬ እና በላዩ ላይ “ልዑል አንድሪው” ተብሎ ከተጻፈበት አሻንጉሊት ጋር “ፎቶግራፍ ለማንሳት በሚል እጁን ጡቴ ላይ አሳርፏል” ማለታቸው ተጠቅሷል ።

እ.ኤ.አ. በ 2022፣ ቨርጂኒያ በ17 ዓመቴ ልዑሉ ጾታዊ ጥቃት አድርሶብኛል በማለት ያቀረበችውን ክስ እንድታነሳ የብሪታንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ሚሊዮን ዶላሮችን መክፈሉ ይታወሳል።

ልዑል አንድሪው ይቺን ሴት አግኝቷት እንደማያወቁ ተናግረዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዚህ የፍርድ ቤት ዶሴ ስማቸው ቢነሳም ሕግ ስለመጣሳቸው የተባለ ነገር የለም።

በመዝገቦቹ መሰረት፣ ኤፕስቲን በአንድ ወቅት ክሊንተን “ልጃገረዶችን በመጥቀስ ወጣት ሴቶች እንደሚወዷቸው” እንደነገራት ዮበርግ መስክራለች።

ክሊንተን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ከ 22 አመት የዋይት ሀውስ የሥራ ተለማማጅ ጋር ግንኙነት ነበራቸው።