
Wednesday, 03 January 2024 20:09
Written by -ልዩ ሪፖርታዥ-

• ከእስራኤል የተመለሰው የልኡክ ቡድን፤ የጉብኝት ሥፍራዎች ሰላማዊና አስተማማኝ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል
• ሁለተኛው የልኡክ ቡድን፣ ለልደት በዓል ወደ እስራኤል ይጓዛል
በብጹዕ አቡነ አብርሃም የተመራው የልዑካን ቡድን፣ በእስራኤል ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊና ቅዱሳን ሥፍራዎችን ለ5 ቀናት ጎብኝቶ፣ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን፤ ሁሉም የጉብኝት ሥፍራዎች ሰላማዊና ምንም ዓይነት ሥጋት እንደሌለባቸው አረጋግጦ መምጣቱን አስታውቋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ የጉዞ ዓላማ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር እስራኤል ከሃማስ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ወዲህ በሚዲያው የሚወራውን በመስማት ብቻ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችም ሆኑ ጉብኝቶች ሙሉ በሙሉ መቆማቸውን የጠቆሙት የልኡካን ቡድን አባላት፤ እዚህ ቁጭ ብሎ ያልተረጋገጠ መረጃ ለምዕመናን ከመስጠት ይልቅ፣ በዓይናችን ዓይተን እውነታውን ለማረጋገጥ ወደ እስራኤል ተጓዝን ብለዋል፡፡
በ5 ቀናት የእስራኤል የቅዱሳን ስፍራዎች ጉብኝት የደረሱበትንና ያረጋገጡትን እውነታ በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ በካፒታል ሆቴል ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡ በመግለጫው ላይ በጉዞው የተሳተፉትና የብጹዕ አቡነ አብርሃም ተወካይ ሆነው የቀረቡትን ጨምሮ በርካታ የአስጎብኚ ድርጅቶች ባለቤቶችና የሥራ መሪዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቶ አለልኝ አድማሱ፣ አሁን በእስራኤል ስላለው ሁኔታና እውነታ አስረድተዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ የጉብኝት ሥፍራዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለማየትና ለመገምገም ነበር ወደ እስራኤል የተጓዝነው ያሉት የልኡክ አባላቱ፤ “በቅድስቲቷ አገር ሁሉም የሚጎበኙ ሥፍራዎች በጣም ሰላማዊና አሁንም መጎብኘት እንደሚችሉ ጎብኝተን አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡
“ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ለጉብኝት ሰላማዊ፣ ምቹና ከስጋት ነጻ መሆኗን አይተናል፤ ከእስራኤል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ማረጋገጫ አግኝተናል” ብለዋል፡፡
ሌላው የጉብኝት ሥፍራዎቹ ሰላማዊ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ነው የሚሉት የልኡክ ቡድን አባላቱ፤ የሄድነውም የተመለስነውም በአየር መንገዳችን ነው ብለዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ በፍልስጤም አስተዳደር ሥር በምትገኘው በቤተልሔም ከተማ ተገኝቶ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቅዱስ ሥፍራ፣ ኖለተ እየተባለ የሚጠራውን የእረኞች መንደርና ሌሎች ቅዱሳን ሥፍራዎች መጎብኘቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አብራርቷል፡፡
ቡድኑ በተጨማሪም፣ ወደ ሰሜን እስራኤል ባደረገው ጉዞ፤ ባህረ ገሊላን፣ታብጋ፣የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን፣ ቅፍርናሆምን ጨምሮ በባህረ ገሊላ ዙሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ቅዱሳን ሥፍራዎችን መጎብኘቱንና በባህረ ገሊላ የጀልባ ጉዞ ማድረጉን አስረድቷል፡፡
“ልኡኩ በተመሳሳይ፣ ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባደገባት በናዝሬት ከተማ ተገኝቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመልአኩ በእዱስ ገብርኤል የተበሰበረችበትን የብስራቱን ቤተ መቅድስ፣ ቤተ ዮሴፍንና የመሳሰሉትን ቅዱሳን ሥፍራዎችን ጉብኝቷል፡፡”
የእስራኤል የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለልኡክ አባላቱ “የእስራኤል የቱሪዝም አምባሳደር” የምስክር ወረቀት በመስጠት አክብሮቱን አሳይቷል ተብሏል፡፡
በብጹዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም ሃገረ ስብከቶች ሊቀ-ጳጳስ የተመራው ይህ ልዑክ፣ በዘርፉ በተሰማሩ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል የሥራ መሪዎችና ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞችን ያካተተ እንደነበር ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ተመሳሳይ ተልዕኮ ያነገበና በአጠቃላይ 70 ገደማ የአስጎብኚና የጉዞ ወኪል መሪዎችን እንዲሁም ምዕመናን ያካተተ ሁለተኛው ልኡክም፣ የልደት በዓልን በኢየሩሳሌም ለማክበር፣ ወደ እስራኤል እንደሚጓዝ ታውቋል፡፡
ልኡኩ በጉዞው፣ በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ፣ በፍልስጤም አስተዳደርና በመላው እስራኤል የሚገኙ ቅዱሳንና ታሪካዊ ሥፍራዎችን እንደሚጎበኝና በዓሉንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እንደሚያከብር በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ይህን የጉዞ ግብዣና የውይይት መድረኮች ያዘጋጀውና ያመቻቸው ተቀማጭነቱን በእስራኤል ያደረገው ቬሬድ ሃሻሮን ጉዞና አስጎብኚ የተባለውና ለረዥም ዓመታት ኢትዮጵያውያን ምዕመናንን እየተቀበለ በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ እንዲሁም በፍልስጤም አስተዳደርና በመላው እስራኤል የሚገኙ ቅዱሳንና ታሪካዊ ሥፍራዎች በማስጎብኘት የሚታወቅ ድርጅት ነው ተብሏል፡፡
አገረ እስራኤልን በዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ከመላው ዓለም እንደሚጎበኟት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡