ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል
+++++++
“መንፈሰ ሰላም ማዕከለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወማዕከለ ቤተ ክርስቲያን… ውእቱ… የሰላም መንፈስ በኢየሱስ ክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ነው::”
(መጽሐፈ ምሥጢር)
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
+++
በዚህ የሕይወት ቃል አማካኝነት የሰላም መንፈስ በኢየሱስ ክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል በየዘመናቱ ያለና የሚኖር መሆኑን እንመለከታለን፡፡ የዚህም መንፈሰ ኃይል በቤተ ክርስቲያን መኖር ሕማመ ነፍስ በሌለበት ምግባረ ሃይማኖት በፍቅር እንድንኖር ለምንሻው ሁሉ እግዚአብሔር በምልዓት በሚከብርበት ቤተ መቅደስ በኩል የሚሰማው የሰላም ጥሪ በማያቋርጠው የመንፈሳዊ ኑሮ ሂደት ለመንፈስ አንድነት፣ ለአካላዊ ሕብረት የሚጠቅም የሕይወት ምሰሶ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ወብነ ክሂል ከመ ንቅትል ኅሊና ሰይጣናዌ …ሰላምን የሚያሳጣ ክፉ ሓሳብን በቤተ ክርስቲያናችን መካከል ባለው ሰላም ከእኛ የማራቅ ችሎታ አለን›› ተብሎ እንደተጻፈው ፍጥረተ ሰብእ ሕይወቱን ለበጎ በሚቀርጸው ሥርዓተ ሃይማኖት በመመራት፣ የሰላምን አስፈላጊነት በትምህርት በድርጊት በመግለጽ ባልተዛነፈ ሰብእና በተሟላ ሰላም መኖር የሚችልበት ክሂል ያለው ፍጡር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ (ዜና አበው)
የሰላም መንፈስ በመካከሏ ሆኖ ከስሕተት የሚጠብቃት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም አመለካከቱ ስሕተት ንግግሩ ሐሰት በሆነው ዓለም የጽድቅና የሰላም ባሕርይ መገለጫ ነው፡፡ ልጆቿ በሰላም በፍቅር በታነጸ ዕለታዊ ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ሰላም የደግነት ሁሉ አክሊል የመንፈሳዊ ምግባራት ዘውድ መሆኑን ስታውጅ መኖሯን የታሪክ መዛግብት፣ ዕውነትን ለመግለጥ የሚተጉ ጸሐፍት ከመቅድም እስከ ህዳግ ይመሰክሩላታል። መሪዋና አጽናኟ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ በተገኘው የሰላም እሴት በእምነታቸው ጸንተው በምግባር በትሩፋት አጊጠው የሚኖሩት ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናንም የረጅም ዘመናት የቅድስና ታሪክ ጉዞዋ ማሳያዎች ናቸው። የእውነትና የሰላም አምድ እንደመሆኗም በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችንና የእርስ በእርስ ደም መፋሰሶች እንዲቆሙ የሰላም ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ ምህላ፣ ጾምና ጸሎት በማወጅ እግዚአብሔር ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን እንዲሰጥ ስትማጸን ቆይታለች። የየዕለት አገልግሎቷም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላም መንፈስ በመካከሏ እንዲሆን አድርጎ ወኃቤ ሰላም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት ስለሆነ በዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የክብር ስፍራውን ይዞ የሚቀጥል ቀዳሚና ዐቢይ ተልእኮዋ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን ።
በመጨረሻም ሰላም የሚጸናው ማንኛውም ማኅበረሰብ እርስ በእርሱ በመተሳሰብና በፍቅር በእውነተኛ መግባባትና በፍትሕ በርኅራሄና በመከባበር አብሮ መኖር ሲቻል ነውና በወንድማማችነት መካከል ጠብን ከሚዘሩ ጥላቻንና መራራቅን ከሚያሰፉ ንግግሮችና ድርጊቶች በመቆጠብ ሁሉም የማኅበረ ሰብእ ክፍል እግዚአብሔር ለሀገራችን ፍጹም ሰላምን ይሰጣት ዘንድ በጸሎት እንዲተጋ ቋሚ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
ከምን ጊዜውም በላይ ሰላምና ፍቅር በሀገራችን እንዲሰፍን በአንድነት ሆነን የምንሠራበት ወቅት ላይ በመሆናችን በመጪዎቹ ዐበይት በዓላት፣ በዘወትሩ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉም በየደረጃው ያላችሁ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና አገልጋዮች “ወፍሬሃኒ ዘጽድቅ በሰላም ይዘራዕ ለእለ ይገብርዋ ለሰላም … የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ ሰዎች በሰላም ይዘራል” በሚለው ሐዋርያዊ ቃል መሠረት በየዐውደ ምሕረቱ ሰላምንና እርቅን በመስበክ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ችግር እንዲወገድ፣ ማኅበራዊ ሰላም እውን እንዲሆን የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ቋሚ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል። ያዕ 3÷18
እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላምን ጽድቅን፣ ፍቅርንና ፍትሕን ይስጥልን
ታኅሣስ 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
** ምንጭ:- የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ