
ከ 5 ሰአት በፊት
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ካበቃ በኋላ በጋዛ ስለሚኖረው አስተዳደር የተያዘውን ዕቅድ ይፋ አደረጉ።
በአካባቢው የፍልስጤማውያን አስተዳደር ውስን እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሐማስ ጋዛን ማስተዳደር እንደሚያቆምና እስራኤል የደኅንነት ቁጥጥሩን እንደምትወስድ አክለዋል።
ይህ ዕቅድ ይፋ ሆኖም ውጊያው ቀጥሏል። ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ በርካቶች መገደላቸው ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በዚህ ሳምንት ወደ አካባቢው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በይዞታ ሥር ባለችው ዌስት ባንክ ከፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን አመራሮች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
ቤይሩት ውስጥ ከፍተኛው የሐማስ አመራር ሳለህ አል-አሮሪ መገደላቸውን ተከትሎ በቀጠናው ውጥረት በነገሠበት ወቅት ነው ብሊንከን የሚጓዙት።
ለግድያው ተጠያቂ እስራኤል ናት እየተባለ በስፋት ይነገራል።
እስራኤል ነገሩ ውስጥ እጇ ስለመኖሩ አላመነችም፣ ነገሩንም አላስተባበለችም።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር “አራት ማዕዘን” አለው ባሉት ዕቅድ፣ እስራኤል የጋዛን የደኅንነት ሁኔታ የምትቆጣጠር ይሆናል።
በዚህ ዕቅድ ጎረቤት አገር ግብፅም ገና ይፋ ያልሆነ ሚና ይኖራታል።
- በደብረ ብርሃኑ የተኩስ ልውውጥ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሆስፒታል ምንጭ ገለጹከ 5 ሰአት በፊት
- ለስራ መነሻ 100 ሺህ ብር በስጦታ የሚሰጡት አቶ ቢጃይ ናይከርከ 6 ሰአት በፊት
- የሁቲ አማጺያን በአሜሪካና አጋሮቿ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው4 ጥር 2024
በዕቅድ ሰነዱ እንደተጠቀሰው ፍልስጤማውያን ግዛቱን የማስተዳደር ሚና ይኖራቸዋል።
“የጋዛ ነዋሪዎች ፍልስጤማውያን ናቸው። ስለዚህ ፍልስጤማውያን የማስተዳደር ሚና ይኖራቸዋል። ይህ የሚሆነው ግን እስራኤልን የሚያሰጋ ሁከት እስከሌለ ድረስ ነው” ብለዋል።
ከጦርነቱ በኋላ ጋዛ ምን ትምሰል የሚለው በእስራኤል አመራሮች መካከል አለመግባባት አስከትሏል።
የእስራኤል የተወሰኑ አክራሪ ቀኝ ዘመም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፓርቲ አባላት እንደሚሉት ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቀው እንዲወጡ መደረግ አለበት።
በአካባቢው አይሁዳውያን መስፈር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
እነዚህ ሐሳቦች “ጽንፈኛ” እና “የማይተገበሩ” በሚል በቀጠናው ካሉ አገራትና አንዳንድ የእስራኤል ደጋፊዎችም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዕቅድ በተሻለ መተግበር የሚችል ቢሆንም በፍልስጤም አስተዳደሮች ተቃውሞ እንደሚገጥመው ይጠበቃል።
ከጦርነቱ በኋላ የጋዛ ነዋሪዎች ግዛቱን ማስተዳደር እንዳለባቸው ሐሳብ መሰንዘሩም አይቀርም።

ኔታንያሁ ስለ ጋዛ እጣ ፈንታ በይፋ ምንም አላሉም።
ሐማስን መደምሰስ ዕቅዳቸው እንደሆነ ገልጸው፣ ጦርነቱ በርካታ ወራት ሊዘልቅ እንደሚችል ተናግረዋል።
በመከላከያ ሚኒስትሩ በተገለጸው ዕቅድ መሠረት፣ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ ወረራ በማካሄድ፣ መተላለፊያ ዋሻዎችን የማፍረስና በእግረኛ ጦር እንዲሁም በአየር ጥቃት የሚቀጥል ይሆናል።
በደቡባዊ የጋዛ ክፍል የእስራኤል ወታደሮች ሐማስን ለማስወገድና ታጋቾችን ነጻ ለማውጣት ውጊያ ይቀጥላሉ ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በሰሜናዊና ደቡባዊ ጋዛ ድብደባ መቀጠሉን ገልጿል። የፍልስጤም ኢስላሚክ ጂሀድ ኦፕሬቲቭ ከፍተኛ አመራር ማምዶህ ሎሎ እንደተገለዱም ገልጿል።
በጋዛ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 125 ሰዎች መገደላቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ከካሃን ዩኑስ በስተምዕራብ በሚገኘው አል-ማዋሲ በተደረገ ጥቃት ዘጠኝ ሕጻናትን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውም ተገልጿል።
ይህ ቦታ ለተፈናቃዮች መጠለያ የሚሆን “ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ” መሆኑን እስራኤል ገልጻ ነበር።
የዐይን እማኙ ጃማል ሐማድ ሳላሕ እንዳለው ተኝተው ሳለ ነው የአየር ጥቃት የተፈጸመው።
“እኩለ ሌሊት ተኝተን ሳለ ካምፑ በአየር ድብደባ ተፈጸመበት። አብዛኞቹ ድንኳን ውስጥ ተኝተው የነበሩት ሕጻናት ነበሩ። 40 ሜትር የተወረወረ አስክሬን አግኝተናል” ብሏል።
በይዞታ ሥር ባሉት የፍልስጤም አካባቢዎች የሴቭ ዘ ችልድረን ኃላፊ ጄሰን ሊ “በጋዛ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም። መጠለያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ቤቶች እንዲሁም ‘ደኅንነታቸው የተጠበቀ’ ተብለው የተከለሉ ቦታዎችም የውጊያ አውድማ ሆነዋል” ብለዋል።
በእስራኤል ድብደባ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ከ22,400 በላይ ናቸው። ይህም ከጋዛ 2.3 ሚሊዮን ነዋሪዎች 1% ማለት ነው።