ዩክሬን

ከ 2 ሰአት በፊት

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታካሄደው ጦርነት የሰሜን ኮሪያን ባለስቲክ ሚሳኤሎች እና ማስወንጨፊያዎች መጠቀሟን አሜሪካ አስታወቀች።

የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ፒዮንግያንግ ለሩሲያ የምትሰጠውን ድጋፍ “አሳሳቢ እና ጦርነት የሚያባብስ” ብለውታል።

አሜሪካ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደምታቀርብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን ለማቀላጠፍ በሚሠሩት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል ተናግረዋል።

ሞስኮ እንዲህ ያለው ትብብር ከፒዮንግያንግ ጋር አለመኖሩን አስታውቃለች።

ዋይት ሃውስ ውንጀላውን ካቀረበ ከሰዓታት በኋላ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው የሚሳኤል ማስወንጨፊያ ተሸከርካሪ ምርት እንዲስፋፋ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ በመስከረም ወር ወታደራዊ ትብብርን በሚመለከት ለመወያየት ሩሲያን ጎብኝተዋል።

ከዚህ ቀደም ፒዮንግያንግን ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ታቀርባለች ስትል አሜሪካ ከሳለች። የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ስለ ባላስቲክ ሚሳኤሎች ዝርዝር መረጃ ሲያካፍል ይህ የመጀመሪያው ነው።

ኪርቢ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሃውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን መግዛቷ በርካታ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን በቀጥታ የሚጥስ ነው።

“ሩሲያ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን በመጣስ ተጠያቂ እንድትሆን እንጠይቃለን” ብለዋል።

ሩሲያ ከኢራን የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን ለመግዛት አቅዳለች የሚል እምነት አሜሪካ ቢኖራትም እስካሁን አለመግዛቷን ገልጸዋል።

ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ የባሊስቲክ ሚሳኤል በመግዛት በዩክሬን መጠቀሟን “በጽኑ እንደምታወግዝ” ዩናይትድ ኪንግደም ተናግራለች።

“ሰሜን ኮሪያ በጠንካራ የማዕቀብ ስር ናት። በዚህም ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ሕገ-ወጥ ጦርነት ሰሜን ኮሪያ በመደገፏ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል ከአጋሮቻችን ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የውጭ፣ የኮመንዌልዝ እና የልማት ፅህፈት ቤት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ኪርቢ በመግለጫቸው የአሜሪካ ኮንግረስ ለዩክሬን የሚሰጠውን ገንዘብ “ሳያዘገይ” እንዲያጸድቅ አሳስበዋል።

“ሩሲያ በዩክሬን ሕዝብ ላይ ለምታደርሰው ዘግናኝ ጥቃት በጣም ውጤታማው ምላሽ ለዩክሬን ወሳኝ የአየር መከላከያ እና ሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎችን ማቅረብ ነው” ብለዋል።

“ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ቆመዋል። ዩክሬናውያን ደግሞ የአሜሪካ ሕዝብ እና ይህ መንግሥት ከእነሱ ጋር መቆማቸውን እንደሚቀጥሉ ማወቅ አለባቸው።”

ለዩክሬን የተሰጠው የመጨረሻው የአሜሪካ ወታደራዊ ዕርዳታ 250 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከቀናት በፊት በዋይት ሃውስ ጸድቋል።

ተጨማሪ የምዕራባውያን ዕርዳታ በቶሎ ካልመጣ የጦርነት አቅሟ እና የሀገሪቱ ፋይናንስ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ዩክሬን አስጠንቅቃለች።