ኢ/ር ቢጃይ ናይከር

ከ 6 ሰአት በፊት

በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ቢጃይ ናይከር ከሰሞኑን መነጋገሪያ ሆነዋል።

ማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ የንግድ ሀሳባቸውን ጣል ሲያደርጉ ይታወቃሉ።

ከሰሞኑን በማህበራዊ የትስስር ገጾች “በዚህ ስራዬ ምረጡኝ” የሚሉ ልጥፎችና የእሳቸው ስም ተበራክተዋል።

ለስራ መነሻ የሚሆን ካፒታል ለማግኘት ‘መደበኛ ባልሆነ መንገድ” በፌስቡክ ውድድር እያካሄዱ ነው።

ለስራ ካፒታል አቅርቦት መደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ዋስትና (ኮላትራል) መጠየቃቸው ብዙ ስራ ፈጣሪዎችን በሀሳብ ብቻ ማስቀረቱ ይነገራል።

ገንዘቡም ሲገኝ ሀሳቡ ያረጃል ይላሉ።

በመሆኑም አቶ ቢጃይ ከፋይናንስ ተቋማት ባለፈ ለስራ መነሻ እንደ እድርና እቁብ ያሉ ሀገራዊ የመረዳጃ ስርዓቶችን አሰራር ለሙከራ እየፈተሹ ናቸው።

ከታህሳስ ወር ገደማ ጀምሮ “ነጻ ፍሬ ፈንድ” የተባለ የስራ ማስጀመሪያ ውድድር በማሕበራዊ የትስስር ገጾች እያካሄዱ ነው።

በአንድ ዙር ለሦስት ቀናት የሚቆየው ውድድሩ በሺህዎች የሚቆጠሩትን ያሳትፋል።

አስተያየት ሰጪዎችም እልፍ ናቸው።

ተወዳዳሪዎች የስራ ሀሳባቸውን አቅርበው በማህበራዊ ገጾች (ፌስቡክ) እና በዳኞች በሚያገኙት ድጋፍና ድምጽ አሸናፊ ሲሆኑ ለስራ ማስጀመሪያ [ሲድ መኒ] 100 ሺህ ብር ከአቶ ቢጃይ ኪስ ያገኛሉ።

ውድድሩ አሁን ላይ ሰባተኛ ዙር ላይ የደረሰ ሲሆን፤ አቶ ቢጃይ እስካሁን ከ600 ሺህ ብር በላይ ለአሸናፊዎች ሰጥተዋል።

አቶ ቢጃይ በስማቸው የተሰየመ ቢጃይ ኢትዮ ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ የተባለ ድርጅት መስራችና ስራ አስፈጻሚ ናቸው።

በ2015 ዓ/ም በንግድ ስራ ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ የነበሩት አቶ ቢጃይ፤ በድርጅታቸው ስራ ያልያዙ ወጣቶችን ያሰለጥናሉ።

ለወጣቶች የሚሰጡትን የተግባር ስልጠና እንዲሁም ስራ መጀመርያ ገንዘብ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ።

“እኔ 100 ሺህ ብር የምሰጠው ዘር ነው። ዘር ለገበሬ ሲሰጥ ማሳውን ይዘራዋል እንጂ አስፈጭቶ አይበላውም። ማሳውን የምትዘሪበት ደግሞ ከምታፍሺው ምርት ትንሹን ነው፤ እና ዝቅተኛውን ነው። ስለዚህ እኔ ዘር ነው የሰጠሁት። ይሄ ፈንድ የዘር ፈንድ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ያ ሰው ከእናቱ ከማሕበረሰቡ ከሌላ ሰው ጨምሮ ሀሳቡን ሊያደርግበት ይችላል፤ ወይም በራሱ ሊሰራበት ይችላል” በማለት ስለሚሰጡት ፈንድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውድድር ጥሪው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚወጣ ሲሆን፤ ጾታን ለማመጣጠንም ለሴቶች ብቻ ውድድር መደረጉን አዘጋጁ ተናግረዋል።

ፈንዱ ‘ብድር፣ ኢንቨስትመንት ወይስ ስጦታ’ ሲል ቢቢሲ የጠየቃቸው አቶ ቢጃይ ናይከር “ስጦታ” ነው ሲሉ መልሰዋል።

በአጠቃላይ ውድድሩ መነቃቃትን ፈጥሯል የሚሉት አቶ ቢጃይ፤ 20 ሺህ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ፈንዱን ለማግኘት እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል።

“. . . ከጦርነትና ከበሽታ [ኮቪድ-19] በኋላ አብዛኛው ወጣት፤ አብዛኛው ሰው ትራውማ [የአእምሮ ቁስለት] ላይ ነው ያለው። ወደ ስራ የሚገባበት [ፍላጎቱ] ይቀንሳል። ስለዚህ [ፈንዱ] ሌላ ሀሳብ እንዲያስቡ ማድረግ ነው አንዱ ዓላማው” በማለት ውድድሩን እንደ ማነቃቂያ ያዩታል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ተፈናቅሎ የነበረው አብዱሰላም ማዕሩፍ የነጻ ፍሬ ፈንድ የመጀመሪያው አሸናፊ ነው።

ራያ አላማጣ ነዋሪ የሆነው አብዱሰላም ከመፈናቀሉ በፊት የባጃጅና የነዳጅ ችርቻሮ ስራ ሲሰራ እንደነበር ይናገራል። ወደ ቀዬው ከተመለሰ በኋላ ግን ስራ አልነበረውም።

“ያለችንን ወረት እዛ [ደሴ] ጨርሰን ነው የመጣነው፤ ራስሽን ለማዳን ስትይ የምትከፍይው መስዋዕትነት ስላለ ማለት ነው” በማለት ስራ ለመጀመር ጥሪት አንዳልነበረው ይናገራል።

ንግድና ስራ ፈጠራ ነክ ጉዳዮችን ስለምከታተል ውድድሩን ፌስቡክ ላይ ነው ያየሁት የሚለው አብዱሰላም፤ “የተዘጋጀ ሀሳብ ስለነበረኝ ወዲያው አስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ አስቀመጠኩ” ይላል።

በዚህም የልብስ ስፌት የስራ ሀሳቡ ተወዳጅነት ያገኘ ሲሆን፤ ለሦስት ቀናት ውድድሩን በመምራትም የዙሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።

በ100 ሺህ ብሩ የስፌት ማሽንና ግብዓቶችን በመግዛት በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ ስራ መግባቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በገንዘቡ መጀመሪያ የገዛሁት ‘ሲንጀር’ የልብስ ሰፌት ማሽን በ33 ሺህ ብር ነው። ከዛ የቀረውን ዲዛይን፤ የተለያየ ቀለም ያላቸውን ጥቅል ልብሶችን ገዘቼ በራሴ ዲዛይን እየሰራሁ የፍራሽ ልብስ፣ የትራስ ልብስ፣ መጋረጃ በመስራት ላይ እገኛለሁ” ብሏል።

የአቶ ቢጃይን የሽልማት ገንዘብ “በትክክለኛ ጊዜ” የመጣ ይለዋል።

ገንዘቡ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ለማስጀመር በቂ አለመሆኑን የሚጠቅሰው አሸናፊው፤ ነገር ግን ስራ አስጀማሪ ነው ይላል።

የአንሶላ፣ ፍራሽና ትራስ ጨርቆችን በራሱ ንድፍ የሚያቀርበው አብዱሰላም ከተለያዩ አካባቢዎች ትዕዛዞችን ተቀብዬ “በደንብ” እየሰራሁ ነው ሲል ይናገራል።

እንደ አብዱሰላም የነጻ ፍሬ ፈንድን ያሸነፉ ሰዎች በተለያዩ ዘርፎች እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት ሸላሚው አቶ ቢጃይ፤ ገንዘቡ በንግድ ሃሰቡ መሠረት በአግባቡ መዋሉን ግን እንደማይቆጣጠሩ ተናግረዋል።

የእስካሁን የጉዞ ሂደቱ ውጤታማ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነጻ ፍሬ ፈንድ ውድድር በሳምንት በአማካኝ ሦስት ጊዜ እየተካሄደ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንደሚዘልቅ ጠቁመዋል።

ይህም ማለት በግርድፉ አቶ ቢጃይ ከሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ለአሸናፊዎች የስራ መጀመሪያ ገንዘብ ይሰጣሉ ማለት ነው።

“. . . እርዳታ ላይ የተመሠረተ ስጦታ ከሚሰጡ ስራና እንቅስቃሴ ላይ፤ ለውጥ ላይ የተመሰረተ ስራ ቢሰጧቸው አንደኛ እነሱንም ሌሎችንም ያስተምራል። ብዙ ነገርም ይጠቅማል የሚል ሀሳብ አለኝ” ሲሉም ቀጣይ ውጥናቸው ሌሎች ሰዎች የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ቢጃይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚዘጋጀው ነጋድራስ የስራ ፈጠራ ውድድር ላይ ዳኛ በመሆን ያገለግላሉ።