የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ልጃቸው ኪም ጁ ኤይ
የምስሉ መግለጫ,የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ልጃቸው ኪም ጁ ኤይ

ከ 3 ሰአት በፊት

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ልትተካቸው የምትችለው ሴት ልጃቸው መሆኗን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም አስታወቀ።

የስለላ ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ዕድሜዋ ከ10-12 የምትገመተዋ ኪም ጁ ኤይ ተተኪ መሪ ልትሆን እንደምትችል የገለጸው።

የመሪው ልጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚሳኤል ሙከራና ወታደራዊ ትዕይንት ከኪም ጆንግ ኡን አጠገብ አብዝታ ትታያለች።

የስለላ ተቋሙ አሁንም ቢሆን ቀጣይ መሪ ማን ይሆናል በሚለው ላይ “ሁሉንም አማራጮች” እየተከታተለ እንደሆነ ገልጿል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የኪም ጆንግ ኡን ልጅ በይፋ የታየችው እአአ በ2022 ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ በአደባባይ በስፋት መታየት ጀምራለቸ።

የስለላ ተቋሙ “በይፋዊ የሕዝብ ክንውኖች ላይ በተደረገው ጥልቅ ምርመራ መሠረት ልጅቷ ቀጣይ መሪ እንደምትሆን ይታመናል” ብሏል።

አያይዞም ኪም ጆንግ ኡን ገና ዕድሜያቸው ስላልገፋና ጉልህ የጤና እክል ስላልገጠማቸው ሁሉንም አማራጮች ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

የ10 ዓመቷ የመሪው ልጅ በዕድሜ ሁለተኛ ትልቋ ልጃቸው እንደሆነች ይታመናል።

የደቡብ ኮሪያ የአንድንት ሚኒስትር ኪም ዩንግ-ሆ፣ ባለፈው ወር በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይ ተተኪዋ መሪ ልጃቸው እንደምትሆን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ልጅቷ እየተሰጣት ያለው ትኩረት የሚጠቁመው ለተተኪነት የተሰጣትን ቦታ ነው” ብለዋል።

“የተከበረችዋ” ልጅ በሚል መጠራት መጀመሯን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ቀድሞ “ተወዳጇ” በሚል ነበር ከሕዝብ ጋር የተዋወቀችው።

በአገሪቱ “የተከበረ” የሚለው አጠራር ከፍተኛ ቦታ ላላቸው ብቻ የተሰጠ ነው።

ኪም ጆንግ ኡን “የተከበሩ ጓድ” ተብለው መጠራት የጀመሩት ተተኪ መሪ እንደሚሆኑ ከታወቀ በኋላ ነበር።

የኪም ቤተሰብ የተከበረ የዘር ሐረግ እንደሆነ ለአገሪቱ ዜጎች ይነገራቸዋል። ይህ ማለትም መምራት የሚችሉት እነርሱ ብቻ ናቸው ማለት ነው።

ኪም ሥልጣኑን ለአራተኛ ትውልድ ነው የሚያስተላልፉት።

ልጃቸው በቅርቡ ሀዋሶንግ 18 የተባለ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ይፋ ሲደረግ አጠገባቸው ነበረች።

ይህ እጅግ ዘመናዊ ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳኤል ነው።

አገሪቱ ማሊግዮንግ 1 የተባለ የስለላ ሳተላይት ስታመጥቅም ከአባቷ ጎን ተገኝታለች።

ይህ ሳተላይት ኪም ጆንግ ኡን ዋይት ሀውስን እንዲመለከቱ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ተንታኞች እንደሚሉት ልጅቷን በሕዝብ ዕይታ ውስጥ መክተት ሥልጣን ላይ እንድትወጣ ማመቻቻ መንገድ ሊሆን ይችላል።

አባታዊ ሥርዓት በተጫናት ሰሜን ኮሪያ ያለውን መድልዎ ለማለፍ መሪው የወወዱት እርምጃ ሊሆን እንደሚችልም የሚናገሩ አሉ። አገሪቱ በሴት ተመርታ አታውቅም።

ስለ ኪም ጆንግ ኡን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው በ2013 የቀድሞው ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ዴኒስ ሮድማን አገሪቱን ከጎበኘ በኋላ ነው።

በባሕር ዳርቻ ከኪም ቤተሰብ ጋር ጊዜ እንዳሳለፈና “ልጃቸውን እንዳቀፈ” ተናግሮ ነበር።

መሪው ስለ ቤተሰባቸው እምብዛም በይፋ አይገልጹም። ከባለቤታቸው ሪ ሶል ጁ ጋር ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ዘለግ ላለ ጊዜ ምሥጢር ሆኖ ቆይቷል።