January 5, 2024 – Konjit Sitotaw
ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ ከተማ አሶሳ ወደ ካማሺ ዞን ዋና ከተማ ካማሽ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ከአምስት ዓመት በላይ እንደኾነው ዋዜማ ሰምታለች።
አንድ የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ መንገዱ ከአምስት ዓመታት በላይ መዘጋቱን አረጋግጠው፣ አልፎ አልፎ በወታደር እጀባ የመንግሥት ኃላፊዎች በተሽከርካሪ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴም ካለፉት ኹለት ወራት ወዲህ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ለዋዜማ ተናግረዋል። መንገዱ መቼ እንደሚከፈት የምናውቀው ነገር የለም ያሉት ኃላፊው፣ ጉዳዩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን የሚመለከት እንደኾነ ጠቁመዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ክልሉን ከኦሮሚያ ጋር በሚያዋስኑት አከባቢዎች የፈጠሩት የጸጥታ ችግር፣ እስካኹንም እንዳልተፈታ ሃላፊው ገልጠዋል።
አንድ የካማሽ ከተማ ነዋሪም፣ ቀደም ሲል ለትራንስፖርት 200 ብር ገደማ ይከፍሉ የነበሩ መንገደኞች፣ ሰሞኑን በተከፈተ አዲስ ተለዋጭ መንገድ ከ1 ሺሕ ብር በላይ ከፍለው ወደ አሶሳ እየተጓዙ መኾኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከአሶሳ ዞን ወደ ካማሽ ከተማ የሚወስደው የመኪና መንገድ፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙትን ነጆ እና መንዲ ከተሞችን ያቋርጣል።