የደቡብ ኮሪያ ጦር
የምስሉ መግለጫ,ደቡብ ኮሪያ በምላሹ ከባድ የጦር መሣሪያ ተኩሳለች

5 ጥር 2024, 16:32 EAT

ሰሜን ኮሪያ ከ200 በላይ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያዋ የዎንፕዮንግ ደሴት መተኮሷን ሴኡል ገለጠች።

ደቡብ ኮሪያ በደሴቷ የሚኖሩ ዜጎች መጠለያ እንዲፈልጉ ካዘዘች በኋላ የራሷን ከባድ መሣሪያ አቀባብላ የተኩስ ልምምድ ስታደርግ ነበር።

ደቡብ ኮሪያ የፒዮንግያንግድ ድርጊት “ጠብ አጫሪ” ስትል የገለጠችው ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ግን የተተኮሱት መሣሪያዎች በደሴቲቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አይደሉም ብላለች።

በአውሮፓውያኑ 2010 በተመሳሳይ ሰሜን ኮሪያ ወደ የዎንፕዮንግ ደሴት ተኩሳ አራት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ከባድ መሣሪያዎቹ የተተኮሱት አረብ ጥዋት በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ከ3 እስከ 5 ሰዓት ሲሆን መሣሪያዎቹ የደቡብ ኮሪያ ድንበር ሳይደርሱ በሁለቱ ሃገራት መካከል ካለ ነፃ ቀጣና ላይ አርፈዋል።

የደቡብ ኮሪያ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ድርጊቱ “በወታደራዊ አቅማችን ላይም ሆነ በሕዘባችን ላይ ምንም ጉዳት ባያደርስም የኮሪያ ባሕረ ገብን ሰላም የበጠበጠና ውጥረት የፈጠረ ነው” ብለዋል።

ፒዮንግያንገ በባሕረ ገቡ መሬት ላይ “በየትኛውም ሰዓት ሊፈጠር ለሚችል ጦርነት” ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ከገለጠች በኋላ ነው ከባድ የጦር መሣሪያ የተኮሰችው።

የዎንፕዮንግ ደሴት ብቻ ሳይሆን የባየንግዮንግ እና ዳየቼዎንግ ደሴት ነዋሪዎችም መጠለያ እንዲፈልጉ ተነግሯቸዋል።

የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስትር ሺን ዎን-ሲክ አርብ ዕለት በለቀቁት መግለጫ “የሰሜን ኮሪያ የጦር መሣሪያ መተኮስ የኮሪያን ባሕረ ገብ መሬት ሰላም የበጠበጠ እና ሰለማዊውን ዞን ያናጋ ነው” ብለዋል።

“ወታደራዊ ኃይላችን በተጠንቀቅ መጠበቅ አለበት። ጠላትን ለመጠራረግ መዘጋጀት ይጠበቅብናል። መልሰው ጠብ እንዳይጭሩ ማድረግ አለበት” ሲሉ አክለዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደቡብ ኮሪያ የራሷን ልምምድ በምታደርግበት ወቅት ከሰሜን ኮሪያ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልነበር ገልጧል።

የሰሜን ኮሪያ ኦፊሴላዊ ዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ባወጣው ዘገባ በምዕራባዊው አቅጣጫ የተደረገው ተኩስ ለጎረቤት ሃገር የተሰጠ “ተፈጥሯዊ ምላሽ” ነው ብሏል።

ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ጀምራ የነበረችውን እንቅስቃሴ ካቋረጠች ወራት ተቆጥረዋል።

የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የሻከረው ባለፈው ኅዳር ፒዮንግያንግ ወደ ሕዋ የስለላ ሳተላይት ካመጠቀች በኋላ ነው።

ይህን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አቋርጣ ድንበር አካባቢ ስለላ ማድረግ እንደምትጀምር መግለጧ ይታወሳል።

ነገር ግን ከዚህ ቀደምም ቢሆን ሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የሚሳዔል ሙከራ ማድረጓ በሁለቱ መካለል ያለውን ቁርሾ አግሎታል።

2 ሺህ ገደማ ሰዎች የሚኖሩባት የዎንፕዮንግ ደሴት የደቡብ ኮሪያ ጦር መቀመጫ ስትሆን ሁለቱ ሃገራት ከሚጋጩበት ሥፍራ በ3 ኪሎ ሜትር ከሰሜብ ኮሪያ ድንበር ደግሞ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።