በዩክሬን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት የወደመ ተሸከርካሪ
የምስሉ መግለጫ,በዩክሬን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት የወደመ ተሸከርካሪ

ከ 7 ሰአት በፊት

ዩክሬን በሩሲያ ከተማ በርካቶች የገደለውን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ሞስኮ ዜጎቿን ከከተማዋ ማስወጣት ጀመረች።

አንድ የሩሲያ ባለስልጣን ከዩክሬን ድንበር ቅርብ ከሆነው ቤልጎሮድ ከተማ በርካታ የቤተሰብ አባላት ወጥተዋል ብለዋል።

ዩክሬን በከተማው ላይ ባደረሰችው ጥቃት ከ25 በላይ ሰዎች ተገድለው ከ100 ያላነሱ ደግሞ መቁሰላቸው ተዘግቧል።

ዩክሬን ይህን ጥቃት የፈጸመችው ሩሲያ 39 ሰዎቸ የገደለውን እና ከ160 በላይ ሰዎች ያቆሰለውን በርካታ የሚሳኤል ጥቃት ከፈጸመች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

የድንበር ከተማው የሚገኝበት ግዛት አስተዳዳሪ ቫይላቼስላቭ ግላደቮክ የከተማው ነዋሪዎች በማሕበራዊ ሚዲያዎች የእርዳታ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር ብለዋል።

“በጣም ሰግተናል። ወደ ሰላማዊ ቦታ ውሰዱን” የሚሉ ጥሪዎችን ተመልክተናል ያሉት ግላደኮቭ፤ አስተዳደራቸው በርካታ የቤተሰብ አባላትን ከከተማዋ ማስወጣቱን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው ነዋሪዎቹ ኦስኮል እና ጉብኪን ተብለው ወደሚጠሩ ከተሞች መዘዋወራቸውን እና በእነዚህ ከተሞችም አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ስለማድረጓ በሩሲያ በኩል ተደጋጋሚ ክስ እየቀረበባት ይገኛል።

ምንም እንኳ ኪዬቭ ወደ ሩሲያ ድንበር ተሻግራ ጥቃት መፈጸሟን ባታምንም፤ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ዩክሬን ድንበር ተሻግራ በሩሲያ ላይ ጥቃት የመፈጸሟ ዜና የተሰማው ሞስኮ ፒዮንግያንግ ስሪት የሆኑ ሚሳኤሎችን እና ማስወንጨፊያዎችን በዩክሬን ጦርነት እየተጠመች ነው የሚል ክስ በቀረበባት ወቅት ነው።

ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ ስሪት የሆኑት ባሊስቲክ ሚሳኤለችን በዩክሬን ጦርነት መጠቀሟ ጦርነቱን የበለጠ ሊያጋግለው እና ውስብስብ ሊያደርገው እንደሚችል አሜሪካ አሳስባለች።

ሞስኮ ግን የፒዮንግያንግ ጦር መሳሪያን በጦርነቱ አልተጠቀምኩም ትላለች።

አሜሪካ በዚህ ጦርነት ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ስለቆሙ ዩክሬናውያን ከአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት የሚያገኙት ድጋፍ መቀጠል አለባት ትላለች።

ለዩክሬን የተሰጠው የመጨረሻው የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ 250 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከቀናት በፊት በዋይት ሃውስ ጸድቋል።

ተጨማሪ የምዕራባውያን ዕርዳታ በፍጥነት የማይደርሳት ከሆነ የጦርነት አቅሟ እና የሀገሪቱ ፋይናንስ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ዩክሬን አስጠንቅቃለች።