ግሊን ሳይመንስ

ከ 7 ሰአት በፊት

ግሊን ሳይመንስ በጓደኛው መኪና ተስላ፣ ኦክላሆማ ውስጥ እየተጓዘ ነው።

70 ዓመቱ ነው። ለግማሽ ምዕተ ዓመት እስር ቤት ቆይቶ ነው የተለቀቀው።

መኪናው ውስጥ ሳለ ሰማዩን እያየ ነበር። እንዲህ በነጻነት ሰማይ ከተመለከተ አስርት ዓመታት አልፈዋል።

ባልፈጸመው ወንጀል ታስሮ 48 ዓመታት በወህኒ ቤት ቆይቷል።

“በጋና ክረምት ሲቀያየር ማየት እስር ቤት ሳሉ አስደሳች አይደለም” ይላል።

እአአ በነሐሴ 2023 ነው ከእስር የተለቀቀው።

በ1974 ካሮላይን ሱ ሮጀርስ የተባለች ሴት ገድሏል ተብሎ ታሰረ። ፍርዱ ግን ትክክለኛ አልነበረም።

በአሜሪካ ታሪክ ያለ ወንጀሉ ረዥም ጊዜ የታሰረው ሰው ግሊን ነው።

ምስክርነት የሰጡ አካላት ሌሎች ተጠርጣሪዎች መጠቆማቸውን ጨምሮ ዐቃቤ ሕግ አለኝ ያለውን ማስረጃ በሙሉ ለተከሳሹ ጠበቆች እንዳላስገባ ከታወቀ በኋላ ነው ፍርዱ የተቀለበሰው።

እሱና ሌላው ተከሳሽ ዶን ሮበርትስ ሲፈረድባቸው ግሊን ገና 22 ዓመቱ ነበር።

መጀመሪያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ከዚያ የዕድሜ ልክ እስራት ሆነ።

አሁን አራተኛ ደረጃ ከደረሰ ካንሰር ጋር እየታገለም ቢሆን ሕይወትን እንደ አዲስ ጀምሯል።

ለ48 ዓመታት ያስቀጠለው ተስፋ “ንጹህ መሆኑ” እንደሆነ ይናገራል።

“ተስፋ አልቆረጥኩም ብል መዋሸት ይሆናል። ግን በድጋሚ ተስፋን አገኝ ነበር” ይላል።

ከአንድ ድግስ ጋር በተያያዘ ከታሰሩ ሰዎች አንዱ ነበር። ፖሊሶች ግን በግድያ ወንጀል ተጠርጣሪዎች ውስጥ ከተቱት።

በአንድ መጠጥ ቤት የምትሠራ ሴት ነበር የተገደለችው። እስካሁን ገዳይ አልተገኘም።

ግሊን ግን ያለ ወንጀሉ ታሰረ።

“21 ዓመት ሞልቶኝ ነበር። የፍትሕ ሥርዓቱን ከዚያ ቀደም አላውቀውም” ይላል።

የመጠጥ ቤት ሠራተኛዋ ስትገደል የነበረች ገዥ ገዳይን ከተጠርጣሪዎች መካከል እንድትጠቁም ብትጠየቅም ግሊን ላይ እንዳልጠቆመች ኋላ ላይ ታውቋል።

ግድያው ሲፈጸም በቦታውም ያልነበረው ግሊን ተፈረደበት።

“ስህተት ነበር። ሆነ ብለው ፍትሕ ነፈጉኝ” ሲል ይገልጸዋል።

ፖሊስ ያልፈታቸው ጉዳዮች በመኖራቸው የተፈጠረውን ጫና እሱን በማሰር ነበር የተወጡት።

ጥቁር አሜሪካውያን ባልፈጸሙት ግድያ የመጠየቅ ዕድላቸው በ7.5 ከፍ ያለ ነው።

እስር ቤት ሳለ “አእምሮን እስከመሳት” እንደደረሰ ያስታውሳል።

በጭንቀት ይታመም ነበር።

ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ደግሞ ወንጀሉን አለመፈጸሙ በይፋ ሳይነገርለት መቅረቱ ያሳስበው ጀመር።

የጉበት ካንሰር እንዳለበት ሲነገረው ደግሞ ነገሮች ተባባሱ።

ያኔ ነው ከእስር ቤት ለመውጣት ያደረገው ትግል የበለጠ የተጠናከረው።

ከእስር ቤት ሲለቀቅ የገና በዓልን ከልጁና ከሦስት የልጅ ልጆቹ እንዲሁም ሰባት የልጅ ልጅ ልጆቹ ጋር ማሳለፍ በመቻሉ ደስተኛ ሆኗል።

“እጅግ ውብ ጊዜ ነበር” ሲል ነው የሚገልጸው።

ሆኖም ግን ይህንን ደስታውን የሚያደበዝዘው ለዓመታት በእስር ቤት ያጠፋው ጊዜ ነው።

የኦክሎሀማ ግዛት ይቅርታ እንዳልጠየቀው ይናገራል።

በዚህ ግዛት ስህተት የታሰሩ ሰዎች 175,000 ዶላር ካሳ ይሰጣቸዋል። ሆኖም ግን ይህንን እስከሚያገኝ ዓመታት እንደሚወስድ ይገልጻል።

በስሙ የገንዘብ ማሰባሰብ እየተካሄደ ሲሆን፣ እስካሁን የተሰበሰበው ገንዘብ 326,000 ዶላር ደርሷል።

ቀሪ ሕይወቱን ማሳለፍ የሚፈልገው ታሪኩን በማካፈልና ለፍትሕ ሥርዓት መሻሻል በመሥራት ነው።

“በነበርኩበት እስር ቤት የነበሩ ሰዎችን መርዳት እፈልጋለሁ” ይላል።

ዓለምን መዞርም ሕልሙ ነው።

“በፍጹም እስር ውስጥ ነበርኩ። አሁን በፍጹም ነጻነት መኖር እሻለሁ” ሲል ሕይወቱን ይገልጻል።

በስህተት መታሰሩ የሚፈጥርበትን ስሜት ወደኋላ ትቶ ለማለፍም እየሞከረ ነው።

“ለ50 ዓመታት ሐዘንና ቁጣ ውስጥ ነበርኩ። ይህ ስሜት ደግሞ ይጎዳል። የሆነው ሆኗል። መለወጥ አልችልም። መቀበል ነው ያለብኝ” ይላል።