የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጅራ ለሽመልስ ሽልማት ሲያበረክቱ
የምስሉ መግለጫ,የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጅራ ለሽመልስ ሽልማት አበርክተውለታል

ከ 9 ሰአት በፊት

የዋሊያዎቹ የመሐል ሜዳ ሞተሩ ሽመልስ በቀለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጫማውን ሰቀለ።

“ብሔራዊ ቡድኑን በምሰናበትበት ወቅት የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል” ብሏል ሽመልስ።

ሽመልስ በቀለ ለብሔራዊ ቡድን 83 ጊዜ የተሰለፈ ሲሆን 16 ጎሎች አስቆጥሮ 13 ለጎል የሚሆኑ ኳሶች አቀብሏል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ካደረጉት ጨዋታ በፊት ለሽመልስ በቀለ ይፋ የአሸኛኘት ዝግጅት ተደርጎለታል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ማግለሉን በማሕበራዊ ሚድያ ገፆቹ ያሳወቀው ሽመልስ ለአድናቂዎቹና ለሙያ አጋሮቹ ያለውን ክብር ገልጧል።

“የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ በተጫወትኩበት አጋጣሚዎች ሁሉ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ያሳለፍናቸውን አጋጣሚዎች ሁሌም የማልረሳቸው እና በታሪክነት የማስቀምጣቸው ናቸው።”

ሽመልስ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰለፈው ከ15 ዓመታት በፊት ሲሆን በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ የነበሩት አብርሀም ተክለማርያም ነበሩ።

ሽመልስ የዋሊያዎቹን ማሊያ ለብሶ ሲጫወት አሠልጣኝ የነበሩትን ሁሉ አመስግኗል።

“ሽሜ” በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የመሐል ሜዳው አውራ ከብሔራዊ ቡድኑ በተጨማሪ ለስምንት የሃገር ውስጥ እና የውጭ ክለቦች ተጫውቷል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል በተጫወቱበት ወቅት ለሽመልስ በቀለ ኦፊሴላዊ አሸኛኘት ተደርጎለታል።

የብሔራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ ከግብፅ በመመለስ ለመቻል በመጫወት ላይ ይገኛል።

ከሴካፋ ዋንጫ የአህጉሪቱ አውራ ውድድር እስከሆነው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ ሃገሩን ወክሎ የተጫወተው ሽመልስ በተለያዩ ውድድሮችና ማጣሪያዎች ተሳትፏል።

ሽመልስ በቀለ በይፋ አሸኛኘት ሲደረግለት

ሜዳ ላይ በሚያሳየው ዲሲፕሊን ከሃገር ቤት እና ከሃገር ውጭ አድናቆትን ያተረፈው ሽመልስ ለብሔራዊ ቡደን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ቢጫ ካርድ የተመለከተው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ የዋሊያዎቹ አባል የነበረው ሽመልስ ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ማግለሉን ሲገልጥ የሙያ አጋሮቹና ደጋፊዎች መልካሙን ተመኝተውለታል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ፍሬው ሰለሞን [ጣቁሩ]፣ መስዑድ መሀመድ፣ ጋቶቸ ፓኖም፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤሊያስ እና ጋዜጠኛ ሀይደር ሸረፋ መልካም ምኞታቸውን ከገለጡ መካከል ናቸው።

አሰልጣኝ ውበቱ “ካሰለጠንኳቸው ተጫዋቾች እጅግ በጣም በስነ-ስርዓት በጨዋነት ከማስባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበርክ። ትልቅ አርአያ የሆነ ባህሪ የነበረክ ተጫዋች እንደነበርክ አስታውሳለሁ” ብለዋል።

“ሁሌም ሜዳ ላይ ልናያቸው ከምንፈልጋቸው አይነት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበርክ የነበረህ አቅም ትልቅ ነበር፤ በምትችለው መንገድ ሀገርህን ስላገለገልክ ክብር ይገባሀል።”

“ካንተ ጋር መጫወት እፈልግ ነበር። ከምወደው ከማደንቀው ተጫዋች ጋር አብሬ በመጫወቴ በጣም ደስ ብሎኛል” ሲል ሱራፌል ዳኛቸው መልካም ምኞቹን ገልጧል።

ሽመልስ ከብሔራዊ ቡድን ግዴታው በተጨማሪ ለበርካታ የግብፅ፣ የሊቢያ፣ ሱዳን እና የሃገር ቤት ክለቦች ተጫውቷል።

ከሃገር ውጭ አልኢተሃድ፣ ኤልጉና እና ምስር ኤልመካሳ የሚጠቀሱ ሲሆን ከሃገር ቤት ሐዋሳ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ይጠቀሳሉ።