የሳሌህ አል-አሩሪ የቀብር ሥነ-ስርዓት
የምስሉ መግለጫ,የሳሌህ አል-አሩሪ የቀብር ሥነ-ስርዓት

ከ 7 ሰአት በፊት

በሌባኖስ መዲና ቤይሩት የተፈጸመውን የሳሌህ አል-አሩሪ የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ ለመታደም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጡ።

ከሦስት ቀናት በፊት ቤይሩት ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል የተባሉት አል-አሩሪ የሐማስ ምክትል የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ።

ትናንት ለቀብር የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሐማስ እና የፍልስጤም ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ ነበር። ጸሎት የሚያደርጉ በርካቶች ነበሩ።

የአል-አሩሪን ሕይወት ለመዘከር መሳሪያዎችን ወደ ሰማይ የሚተኩሱም በርካቶች ነበሩ። የሐማስ መሪዎች ደግሞ የበቀል እርምጃ ለመወሰድ ሲዝቱ ተሰምተዋል።

እስራኤል ይህን ከፍተኛ ሐማስ መሪን ቤይሩት ውስጥ መግደሏን ባታምንም፤ አል-አሩሪን አልገደልኩም አላላችም።

ሐማስ ግድያውን ያወገዘ ሲሆን ሂዝቦላህ ደግሞ በሊባኖስ ሉዓላዊነት ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ሲል ክስተቱን ገልጾታል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው እስራኤል “ሊባኖስን ወደ… ግጭት ለመክተት” እየሞከረች ነው ብለዋል።

እስራኤል ከዚህ ቀደም የሐማስ መሪዎችን ዒላማ ስታደርግ ብትቆይም አል-አሩሪን ሌባኖስ ውስጥ መግደሏ የአገሪቱን ሉዓላዊትን የሚገዳደረው ነው ሲሉ ሌባኖስ እና ሄዝቦላ እርምጃውን አጥብቀው ተቃውመዋል።

የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ የሆኑት ሃኒያህ ጥቃቱን “አሳፋሪ… የሽብር ተግባር፣ የሊባኖስን ሉዓላዊነት የጣሰ እና የጦርነት ቀጠናው ለማስፋፋት ያለመ” ሲሉ ጠርተውታል።

ሂዝቦላህ የአሩሪ ሞት “በሊባኖስ፣ በሕዝቦቿ፣ በደኅንነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና በተቋሞቿ ላይ የተፈጸመ ከባድ ጥቃት ነው” ብሎ እንደሚቆጥረው ገልጿል።

ምክትል የሐማስ መሪ እንዲሁም በሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በሆነው አል-ቃስም ብርዴድ ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበሩት የአል-አሩሪ ሞት ለሐማስ ትልቅ ኪሳራ ሆኖ ተወስዷል።

የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት አል-አሩሪ የተገደሉት በደቡባዊ ቤይሩት በእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ነው። ጥቃቱ ከአል-አሩሪ በተጨማሪ ሌሎች 6 የሐማስ ወታደራዊ አዛዦችን እና የቡድኑ አባላትን ገድሏል።

ግድያው ግጭቱን በቀጠናው ወደ ሰፊ ደረጃ እንዳይወስደው ስጋት ፈጥሯል።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ

የሄዝቦላ መሪ ሐሰን ነስራላህ በቀጣይ ሊወስዱት የሚችሉት እርምጃ የበርካቶችን ቀልብ ይዟል። ከግድያው በኋላ ነስራላህ ባደረጉት ንግግር ለአል-አሩሪ ግድያ እስራኤል ቅጣቷን ትቀበላለች ብለዋል።

“ጠላት በሌባኖስ ላይ ጦርነት ማወጅን ካሰበ፤ ውጊያችን በሕግ እና ድንበር የሚገደብ አይሆንም” ብለዋል ነስራላህ።

በኢራን የሚደገፈው እና መቀመጫውን ሌባኖስ ያደረገው ሄዝቦላ ከሐማስ በላይ የተደራጀ ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ያለው ሲሆን ለእስራኤል ስጋት ሊሆን የሚችል ቡድን ነው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሚሳኤሎችን የታጠቀው ቡድን ዋነኛ ዓላማ የእስራኤል መጥፋት ነው።

ከእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መጀመር አንስቶ ሄዝቦላ በሰሜናዊ እስራኤል አካባቢዎች ጥቃቶችን ሲፈጽም ቢቆይም ወደ ጦርነቱ በሙሉ አቅሙ አልገባም። እስራኤል ለእነዚህ ጥቃቶች ምላሽ ስትሰጥ ብትቆይም ግጭቱ በእስራኤል እና ሌባኖስ ድንበር አካባቢ ተገድቦ ቆይቷል።