737 ማክስ 9

ከ 6 ሰአት በፊት

መነጋገሪያነቱ የቀጠለው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ አንድ የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ከበረራ አገደ።

የአሜሪካው አላስካ አየር መንገድ በቁጥር 65 የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖቹን ያገደው በበረራ ወቅት የአንደኛው አውሮፕላን መስኮት ተገንጥሎ አውሮፕላኑ በአስቸኳይ ለማረፍ ከተገደደ በኋላ ነው።

ትናንት አርብ በኦሬጎን ግዛት ከፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ሲበር የነበረው አውሮፕላን የገጠመውን አደጋ ተከትሎ ከ35 ደቂቃዎች በረራ በኋላ በመነሻው ለማረፍ ተገዷል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩት 177 ተሳፋሪዎች እና ሠራተኞች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው አውሮፕላኑ በሰላም አርፏል ብሏል።

የአደጋው መንስዔ እስኪጣራ ድረስ ሁሉንም 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከበረራ እንዳገደ አየር መንገዱ አስታውቋል።

ይህ ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን ባለፉት ዓመታት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አደጋ ምክንያት ከበረራ ታግዶ የነበረው ይህ ማክስ 737 ዝርያ መሆኑ ይታወቃል።

ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ አየር መንገዶች በ737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓት ውስጥ ሊላላ የሚችል ብሎን ላይ ፍተሻ እንዲያደርጉ በአምራቹ ቦይንግ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ነበር።

ትናንት በአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ ቦይንግ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት እየሰራሁ ነው ብሏል።

የበረራ መቆጣጠሪያ ፍላይትራዳር24 እንዳሳየው አውሮፕላኑ አደጋው ያጋጠመው 16ሺህ ጫማ (4ሺህ ሜትር ገደማ) ከፍታ ላይ ሳለ ነበር።

ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከአውሮፕላኑ ክንፍ እና ሞተር ጀርባ የነበረው መስኮት መገንጠሉን ተከትሎ በአውሮፕላኑ የመሃል ክፍል ላይ ትልቅ ክፍተት ተፈጥሮ አሳይተዋል።

እንደ መታደል ሆኖ ከተገነጠለው መስኮት ጎን የተቀመጠ ተሳፋሪ አልነበረም ተብሏል።

የአሜሪካ የትራንስፖርት እና ደኅንነት ቦርድ በኤክስ ገጹ ክስተቱን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

እንደ ቦይንግ አሃዝ ከሆነ ወደ 1ሺህ 300 የሚጠጉ አውሮፕላኖች በመላው ዓለም ለሚገኙ አየር መንገዶች ተላልፈዋል።