January 6, 2024 – Konjit Sitotaw

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሱማሌላንድ ጋር በባሕር በር ዙሪያ በደረሱበት የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ ከሱማሊያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ወደ ሞቃዲሾ ስልክ ደውለው ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን ከኢጋድ ምንጮች ሰምቻለኹ ሲል ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ የሱማሊያን የግዛት አንድነት የመጣስ ፍላጎት እንደሌላት ለሞቃዲሾ ባለሥልጣናት ለማስረዳት ፈልገው እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል። ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ዝርዝር ይዘት በጽሁፍ እስካኹን ይፋ አላደረጉም።
የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ የኢትዮጵያ መሪዎች ከሱማሊያ ግዛት የባሕር በር አግኝተናል ብለው ሕዝባቸውን ከማሳሳት ቢቆጠቡ ይሻላል በማለት መናገራቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ኢትዮጵያ በሱማሊያ ምድር የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ ያልተደረገና ወደፊትም ሊደረግ የማይችል ነው ማለታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ስምምነቱን መፈራረማቸውን ተከትሎ ለሱማሊያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አጋርነታቸውን ከገለጡት መካከል፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ቱርክ፣ ግብጽ፣ አውሮፓ ኅብረትና ዓረብ ሊግ ይገኙበታል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ እውቅና በመስጠት ጉዳይ ላይ ከውሳኔ የምትደርሰው የመጨረሻው የባሕር በር ስምምነት ተፈርሞ የባሕር በሩን ስትረከብ እንደኾነ ለመንግሥታዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል። ሬድዋን፣ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይልና ለባሕር ንግድ ማዕከል መገንቢያ እንደምታገኘው የሚጠበቀው ቦታ በበርበራና ዘይላ ወደቦች መካከል እንደሚገኝ ገልጸዋል። ቦታው ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር በባቡርና የብስ መንገድ እንዲገናኝ ስምምነት ላይ እንደተደረሰም ሬድዋን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በምላሹ ለሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዛቱ ወደፊት የሚወሰን ድርሻ ለመስጠት መስማማቷን የገለጡት ሬድዋን፣ የድርሻው ብዛት የሚወሰነው ኢትዮጵያ ወደፊት ለባሕር በሩ ለመክፈል በምትስማማው የሊዝ ኪራይ መጠን ላይ እንደሚኾን ተናግረዋል።
