January 8, 2024 – EthiopianReporter.com 


በድርቅ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙት ወ/ሮ ወለተማሪያም ወልደዮሐንስና እርዳታ የሚፈልጉ የአበርገሌ ነዋሪዎች በከፊል

ማኅበራዊ በትግራይ ክልል አበርገሌ ወረዳ 91 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተነገረ

ዮናስ አማረ

ቀን: January 7, 2024

በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ በ120 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው አበርገሌ ወረዳ ድርቅ ባስከተለው የረሃብ አደጋ፣ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 91 መድረሱን ወረዳው አስታወቀ፡፡

በወረዳው ባሉ 13 ቀበሌዎች ድርቁ ያስከተለውን የመኸር ምርት ውድመትንና የተጎጂዎችን ቁጥር ከፌዴራልና ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ለጋሾች ጋር በመሆን ጥናት ማድረጉን የገለጸው ወረዳው፣ በረሃብ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ወገኖች ቁጥር ወደ 93 ከፍ ሊል እንደሚችል አመልክቷል፡፡

በትግራይ ክልል ተካሂደው በነበሩ ውጊያዎች ዋነኛ ግንባር ከነበሩ አካባቢዎች አንዱ የነበረው ወረዳው ከድርቅ በተጨማሪ ጊዜውን ባልጠበቀ ውርጭና ዝናብ፣ በተባይ፣ እንዲሁም በግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት ችግር ሲፈተን መቆየቱ ተነግሯል፡፡ ከወረዳው 13 ቀበሌዎች በተለይ እንደ ፈለገ ሕይወት፣ ስዩ፣ ተክለ ወይኒና ግራውር የመሳሰሉት ቀበሌዎች ከባድ የዝናብ እጥረት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡

ሪፖርተር በተለይ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ አላገኘም በተባለው የፈለገ ሕይወት ቀበሌ ተገኝቶ የጉዳቱን ሁኔታ በአካል ተመልክቷል፡፡ በቀበሌው ባሉ የተለያዩ ጣቢያዎች በምግብ እጥረት ሰውነታቸው የተጎዳ ሰዎችን ለማየት የተቻለ ሲሆን፣ አስተያየት የተጠየቁ ነዋሪዎችም የምግብ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአበርገሌ ወረዳ ግብርና ቢሮ ሥር ያለው የአደጋ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍል ኃላፊ አቶ ኃይለ ኪሮስ ብርሃኑ፣ ወረዳው የገንዘብ ሳይሆን አጣዳፊ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የገንዘብ ድጋፍ ቢመጣ እህሉ ከየት ይገዛል? አሁን ገንዘብ ሳይሆን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ካላገኘን የብዙ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ ይቀጥላል፤›› ሲሉ የተናገሩት ኃላፊው፣ ወረዳው አጣዳፊ ዕርዳታ እንዲደረግለት ጠይቀዋል፡፡

ረሃቡን ሽሽት ወደ ሌላ አካባቢ ተፈናቅለው የነበሩ የፈለገ ሕይወት ቀበሌ ነዋሪዎች ዕርዳታ ይሰጣል ሲባል ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን አስረድተው፣ ይሁን እንጂ ከሦስት ሳምንት ቀደም ብሎ ለሕይወት ማቆያ የምግብ ዕርዳታ ቢያገኙም ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ የሚያደርግ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡

የሚደግፋቸው ልጅም ሆነ ሌላ ቤተሰብ የሌላቸው ወ/ሮ ወለተ ዮሐንስ ወልደ ዮሐንስ አረጋዊት የ1977 ዓ.ም. ጨምሮ ብዙ ድርቆች እንዳዩ ይገልጻሉ፡፡ ከበድ ያለ ረሃብ ሲከሰት ወደ ተከዜ ሸለቆ ወንዝ ዳር በመውረድ ራሳቸውንም እንስሶቻቸውንም ከአደጋ ለማዳን መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹አሁን ግን ድርቁ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱም በመከሰቱ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሕይወትን ማቆየት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ተከዜን ተሻግረው ከአሥር ዓመት በላይ ወልቃይት አካባቢ የኖሩት አረጋዊቷ፣ ጦርነቱ ሲከሰት ከዚያ ተፈናቅለው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ልጅም ሆነ የሚረዳ ሰው የለኝም፤›› የሚሉት እኚህ እናት የመንደሩ ሰዎች በየተራ አዋጥተው በሚሰጧቸው ምግብ ሕይወታቸው መቆየቱን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ባለሀብቶችና አንዳንድ በግልም በቡድንም ዕርዳታ የሚያሰባስቡ ለጋሾች ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን በቆሎ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ዱቄትና ፋፋ የመሳሰሉ የምግብ ዕርዳታዎች እንደላኩላቸው ተጎጂዎች ተናግረዋል፡፡

የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪና በዕድሜ አንጋፋ የሆኑት የፈለገ ሕይወት ነዋሪ አቶ ተክሌ ተወልደ፣ ‹‹በ1977 ዓ.ም. ቢርበንም አካባቢያችን ሰላም ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ወደ ሁመራም፣ ወደ ተከዜም፣ ወደ ወልቃይትም ተሰዶ ሕይወት ማቆየት ይቻል እንደነበር የበፊቱን በማስታወስ ከአሁኑ ጋር ያስታወሱት አቶ ተክሌ፣ ‹‹አሁን ግን መሄጃ አጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ ጥቂት የትግራይ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ዕርዳታ እንደላኩ መስማታቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹አደጋው ከባድ በመሆኑ በረሃብ ከማለቃችን በፊት መንግሥት ይድረስልን፤›› ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

በአበርገሌ ወረዳ በድርቅ አደጋው የተነሳ ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ከ46 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሰደዳቸውን ወረጃው አስታውቋል፡፡ በረሃብ ሞቱ ከተባሉት 91 ሰዎች በተጨማሪ 394 ሰዎች በምግብ እጥረት በመዳከማቸው የአካል ጉዳት እንደገጠማቸው ተነግሯል፡፡

ከተከዜ ወንዝና ከተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ የሚዋሰነው የትግራይ ክልል አበርገሌ ወረዳ፣ ከወንዝ ማዶ ካለው የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ ወረዳ ኩታ ገጠም መሆኑ ይነገራል፡፡ ከወንዝ ማዶ በሚገኙ እንደ ሰቆጣ ባሉ አካባቢዎችና በሌሎችም አካባቢዎች ከባድ ድርቅ መከሰቱ ከተነገረ ከራርሟል፡፡

የተከዜ ወንዝን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተፋሰሶች የሞሉበት ይህ አካባቢ ከፍተኛ የመስኖ አቅም ቢኖረውም፣ ነገር ግን በተደጋጋሚ ድርቅ ሲጠቃ መቆየቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡