EthiopianReporter.com 

ዜና በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከአምስት ሺሕ በላይ ታራሚዎች ከማረሚያ…

አበበ ፍቅር

ቀን: January 7, 2024

በአማራ ክልል በመከላከያና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ከአምስት ሺሕ በላይ ታራሚዎች ከእስር ቤት መውጣታቸውን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ታራሚዎቹ በክልሉ ውስጥ ካሉ ሰባት ማረሚያ ቤቶች መውጣታቸውን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አባተ ቢሻው (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ካለበት ችግር አኳያ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች የሎጀስቲክ አቅርቦትን ለማጓጓዝ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጹት አባተ (ዶ/ር)፣ ፍኖተ ሰላም በነበረው ችግር ለታራሚዎች ምግብ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ታራሚዎች መለቀቃቸውን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡

ታራሚዎቹ የተፈቱት የፍኖተ ሰላም የማረሚያ ቤት አስተዳደር እንዲፈቱ ባቀረበው ጥያቄና በኅብረተሰቡ አስተያየት መሠረት ተነጋግረው እንዲወጡ መደረጉን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት ለታራሚዎች የበጀት ማሻሻያ ተደርጓል ያሉት አያሌው (ዶ/ር)፣ በይቅርታ የሚለቀቁትም በዓላትን ጠብቀው ይቅርታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በይቅርታ የሚለቀቁ ታራሚዎች ወደ ቤተሰብ በሚቀላቀሉበት ወቅት በቅድሚያ ከተበዳይ ጋር ዕርቅ እንዲፈጽሙ እንደሚደረግ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት የተለያዩ ሙያዎችን ተምረው ስለሚወጡ ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት እንዲተዳደሩ ይደረጋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ታራሚዎች በይቅርታ ወደ ቤተሰብ የሚቀላቀሉበትን መንገድ ለማሻሻል አዲስ ዕቅድ መጀመሩን የጠቆሙት አያሌው (ዶ/ር)፣ ከዚህ በፊት ታራሚዎች ተጠሪነታቸው ለአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳይ የነበረውን ሕግ በማሻሻል፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደር አዋጅ በሚል ተጠሪነቱን ለፍትሕ ቢሮ የሚሆንበት ረቂቅ መጠናቀቁን አክለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከሁለት ሺሕ በላይ ታራሚዎች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል በይቅርታ ከማረሚያ ቤት ወጥተው የነበሩና ሦስት ዓመት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ 38 ግለሰቦች የተሰጣቸው ይቅርታ ተነስቶ በሕግ እንዲጠየቁ መደረጋቸው ተመላክቷል፡፡