EthiopianReporter.com 


የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አገልገሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት

ዜና በሐሰተኛ ሰነድ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ቀጥረው የሚያሠሩ መኖራቸው ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 7, 2024

በሐሰተኛ መረጃ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችንና ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ግለሰቦች ቀጥረው የሚያሠሩ መኖራቸውን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አገልገሎት አስታወቀ፡፡

የአገልገሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ ሰነዶችን መሠረት አድርጎ መኖር የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ተቋማቸው ባደረገው ማጣራት ከ18 ሺሕ በላይ ሐሰተኛ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ከ1,500 በላይ ሐሰተኛ ቪዛ፣ ከ1,800 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የተገኘ ሲሆን፣ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች የተሳሳተና ሐሰተኛ ይዘት ያለው የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘው ተገኝተዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የድርጅት ምዝገባ ሳያከናውኑ የሚገኙ አካላት መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቢዝነስ መሰል ድርጅት እንዳላቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ እውነታው ግን ድርጅተ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይኖር የውጭ ዜጎች እንዲገቡ እየተደረገ ቪዛ የሚሰጥበት ሒደት መኖሩን ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

አንድ የውጭ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ሠራተኛ ሲያስገባ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት ቀድሞ ማስመዝገብ ያለበት ቢሆንም፣ ይህ ሳይደረግና የድርጅት ምዝገባ ሳያከናውኑ በውሸት መረጃ የውጭ ዜጎችን ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ ባልተፈቀደ የሥራ መስክ የሚያሰማሩ አካላት መኖራቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በቀጣይ ተጨማሪ ማጣራት በማድረግ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ይጀመራል ያሉ ሲሆን፣ ሕጋዊ መረጃ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች በአንድ ወር ማለትም ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት በመምጣት ሕጋዊ ሰነድ መያዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ ሥራ በዘመቻ መልክ ለተወሰነ ጊዜ መሠራት አለበት ተብሎ በመንግሥት የታመነበት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የውጭ ዜጎች እንቅስቃሴ ሁሉ በሕጉ መሠት መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚኖሩና ቋሚም ሆነ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሐሰተኛ ሰነድ ብቻ በመያዝ እንደሚንቀሳቀሱ ተገልጿል፡፡ ከሐሰተኛ ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በተጨማሪ ሐሰተኛ ፓስፖርት፣ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ፣ ሐሰተኛ ቪዛና መሰል የሠራተኛ ሰነዶችን ይዘው ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ሰዎች መካከል ሲገቡም በየት እንደገቡ የማይታወቅ፣ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የገቡበትን ሥራ ትተው ሌላ ሥራ ላይ የሚገኙ እንዳሉ ገልጸው፣ ይህ ድርጊት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ውስጥ ከሌሎች ተቋማት እንደተላኩ ተደርገው የተጻፉ በርካታ ሐሰተኛ ደብዳቤዎችና የሥራ ፈቃድ መረጃዎች መገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

በዘመቻ የማጣራት ሥራው ወደ ኢትዮጵያ ለሥራና ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ዜጎችን የሚመለከት ሲሆን፣ አገሪቱ የምታስተናግዳቸውን ስደተኞች የሚያካትት አይደለም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያዊ ዜግነት አሰጣጥን በተመለከተ በርካታ ብልሹ አሠራሮች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ይህንን ሊያጣራ የሚያስችሉ መሥፈርቶች እየተጨመሩ መሆናቸውን ወ/ሮ ሰላማዊት ተናግረዋል፡፡

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሰዎችን ማንነትና ለማጣራት የሚጠቅሙ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮች እየተዘረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት ከሚታየው የፓስፖርት አሰጣጥ ችግር ጋር በተገናኘ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በርካታ የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት ትክክለኛ ባልሆነ አሠራር አስመስለው በመሥራት፣ በአገር ውስጥ ተቋማት ለአገልግሎት ሲጠቀሙበትና በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱበት መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱ ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ የውጭ አገር ዜጎች እንዲመዘገቡ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ 70 ሺሕ ያህል ግለሰቦች መመዝገባቸው ተገልጾ ነበር፡፡