

እሸቱ ከበደ (ዶ/ር)ና ወ/ሮ ሀና አርዓያ ሥላሴ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ
ማኅበራዊ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለወንጀል ተጋላጭ ለሆኑ ሰነዶች የበይነ መረብ አገልግሎት አልሰጥም…
ቀን: January 7, 2024
- የትምህርት ጉዳዮችን በበይነ መረብ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት፣ ለወንጀል ተጋላጭ ለሆኑ ለፓስፖርት፣ ለመታወቂያና ለተለያዩ የውል ሰነዶች አገልግሎቱን በበይነ መረብ እንደማይሰጥ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በአጠቃላይ የትምህርት ጉዳዮችን በበይነ መረብ አገልግሎት መስጠት የጀመረበት ዋነኛ ምክንያት፣ በርካታ ተገልጋዮች ‹‹የትምህርት ማስረጃ ይረጋገጥልኝ›› ጥያቄ በአካል ተገኝተው በመጠየቃቸው ምክንያት እንደሆነ፣ ከኢትዮጵያ ፖስታ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አብዛኛዎቹ ተገልጋዮች የትምህርት ማስረጃ ይረጋገጥልኝ ጥያቄን ወደ ተቋሙ በሚያመጡበት ወቅት የማስተናገድ ችግር ይታያል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከታኅሳስ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የተቋሙን አሠራሮች የማዘመን፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ ተከናውኖ በአሁኑ ወቅት ሥራ መጀመሩን አክለው ገልጸዋል፡፡
በፍርድ ቤት ስም በማስቀየር ምክንያት በፓስፖርት፣ በመታወቂያ፣ በተለያዩ የውል ሰነዶች ላይ ወይም በቤተሰብ የውርስ ሰነዶች ላይ ካለው ስም ጋር ለማመሳሰል ለሚፈልጉ ተገልጋዮች፣ አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተለያዩ ተቋማት የነባር ሠራተኞቻቸውን ወይም አዲስ የሚቀጥሯቸውን ግለሰቦች የትምህርት ሰርተፍኬት ትክክለኛ ወይም ሐሰተኛ መሆኑን ለማጣራት የሚያገለግል ማስረጃ ማጣሪያ (Document Verification) አሠራር፣ በበይነ መረብ አገልግሎቱ ተግባራዊ እንደሚሆን እሸቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል አንድ ግለሰብ የትምህርት ማስረጃውን ለሌላ ተቋም መላክ ቢፈልግ፣ ተቋሙ ባስቀመጠው አሠራር መሠረት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል ገልጸው፣ ተገልጋዮች በበይነ መረብ የሚመርጧቸውን አገልግሎቶች በኢትዮጵያ ፖስታ በኩል ሰነዶችን መቀበል የሚችሉበት አሠራር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ ሲስተም መሠረት ማናቸውም አገልግሎት ፈላጊዎች በአካል ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይኖርባቸው ባሉበት ሆነው፣ በተለያዩ አማራጮች የሚፈለገውን አገልግሎት በዲጂታል ማግኘት የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ለትምህርት ምዘናና ለምርምር ለሚያስፈልጉ መረጃዎች በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ቁጥር ባላቸው የትምህርት ተቋማት የተመለመሉ የትምህርት ባለሙያዎች የሚሰማሩ መሆናቸውን፣ ባለሙያዎቹ የሚሰበስቡት መረጃ ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ እንዲቀመጥ መደረጉን አክለዋል፡፡
ከዚህ በፊት አገልግሎት ፈላጊዎች በአካል ሲገኙ ረዥም ሠልፍ እንደነበር፣ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ቀጠሮ በመጠበቅ ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጉ ስለነበር ይህ ዘመናዊ አሠራር ተዘርግቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የዘረጋውን ፕላትፎርም በመከተል ማንኛውም ተገልጋይ ከ700 በላይ በሚሆኑ የኢትዮጵያ ፖስታ ቅርንጫፎች በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ያሉት፣ የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀና አርዓያ ሥላሴ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ለረዥም ዓመታት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ180 አገሮች ተደራሽ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም አገልግሎት በዓመት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዕቃዎች የሚያንቀሳቅስ መሆኑን፣ የተለያዩ ዕቃዎችንም ሆነ ሰነዶችን ለተገልጋዮች በተገቢው መንገድ በማድረስ የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል፡፡
