EthiopianReporter.com 

ዜና ቦሌ ኤርፖርት አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችልበት አቅም እንዲገነባ ተጠየቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 7, 2024

መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገውና ቮይስ ፎር ፕሪዝነርስ (Voice for Prisoners) የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ በርካታ አደንዛዥ ዕፆች ይተላለፉበታል ባለው በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመዘርጋት አቅሙ እንዲገነባ ጥያቄ አቀረበ፡፡

በተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. በ2023 መነሻቸውን ኬንያ፣ ዴንማርክ፣ ታይላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኔዘርላንድስ፣ ናምቢያ፣ ህንድና ዚምባቡዌ ያደረጉ፣ ከአዲስ አበባ ሆንግ ኮንግ ሲጓጓዙ የነበሩ አሥር ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውን የገለጹት ሆንግ ኮንግ በሚገኝ እስር ቤት የሚያገለግሉት የድርጅቱ ኃላፊ ጆን ዎተርስፑን ናቸው፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች አደንዛዥ ዕፅ በሰውነት ክፍላቸውና በሻንጣቸው ከተው ሲጓጓዙ በመገኘታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ከእነዚህ በተጨማሪ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ጭምር በርካታ ዝውውሮች እንዳሉ እንረዳለን፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት በዓለም ላይ ካሉ ኤርፖርቶች ለዕፅ አዘዋዋሪዎች ቀላሉ መስመር መሆኑን፣ አደገኛ ዕፆችን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅና ወንጀል ጉዳዮች ቢሮ (UNODC) ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የቦሌ ኤርፖርት ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ፣ ላቲን አሜሪካና እስያ የዕፅ ዋነኛ ማመላለሻ መስመር ነው፡፡ በተቋሙ የተሠራው እ.ኤ.አ. የ2023 የዓለም አደንዣዥ ዕፅ ዝውውር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በብራዚል ከተያዙ 165 ኮኬይን አዘዋዋሪዎች መካከል 64 ያህሉ መዳረሻቸው አዲስ አበባ ነበር፡፡

የቮይስ ፎር ፕሪዝነርስ ኃላፊ ጆን ዎተርስፑን እንደሚሉት፣ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የዕፅ መዘዋወሪያ መስመሮች ከሚባሉት መካከል ሳኦፖሎ፣ ጆሃንስበርግና አዲስ አበባ በቀዳሚነት ደረጃውን ይይዛሉ፡፡

‹‹መንግሥትን እየወቀስን ሳይሆን እየጠየቅንና እየለመንን ነው፡፡ ሰዎች በአደንዘዥ ዕፅ ዝውውር ምክንያት በቁጥጥር ሥር እየዋሉ፣ ትዳር እየፈረሰ፣ ልጆች እየተበተኑ፣ ንፁኃን ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤት ውስጥ እየተጣሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በተደጋጋሚ ከመንግሥት ተቋማት ጋር በሚያደርጉት ውይይት አዎንታዊ ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ በሚጠበቀው ልክ እየተሠራ ባለመሆኑ የዕፅ ዝውውሩ በከፍተኛ ደረጃ አሁንም እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ እየታየ አይደለም ብለዋል፡፡

በቦሌ ኤርፖርት ቢያንስ የሠለጠኑ ውሾችን በማሰማራት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ይቻላል የሚሉት ጆን ዎተርስፑን፣ ጉዳዩ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በጥብቅና በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ኤርፖርት በሕገወጥ መንገድ የቁም አንስሳት፣ ገንዘብ፣ የተከለከሉ ምግቦች የሚያዘዋውሩ እንዳሉ መረጃ እንዳላቸው፣ ነገር ግን ከሁሉም የባሰው አደገኛ ዕፅ ዝውውር ጉዳይ በአፅንኦት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡

ጆን ዎተርስፑን አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር በቁጥጥር ሥር ከሚውሉት መካከል በርካቶች ሴቶች ሲሆኑ፣ መረጃ ሳይኖራቸው ዕፁን ይዘው እንዲጓጓዙ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሳያውቁና ያለ ወንጀላቸው የታሰሩትን ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ የቦሌ ኤርፖርት ቁጥጥሩ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ አሳስበዋል፡፡