EthiopianReporter.com

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

January 7, 2024

በናርዶስ ዮሴፍ

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በአስመጪዎች በቀረቡለት የባንክ ፈቃድ ሰነዶች አጠቃቀም ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ከተመለከተ በኋላ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሦስት የተለያዩ ውሳኔዎች ማለትም ታክስ ከከፈሉ በኋላ፣ የቀረጥና የታክሱን መጠን አሥር በመቶ ቅጣት እንዲከፍሉና ንብረታቸውን እንዲረከቡ ወይም በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅና በአዋጅ ቁጥር 859/2006 መሠረት እንዲወረሱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ሪፖርተር የተመለከታቸው በ2015 ዓ.ም. በመስከረም፣ በግንቦትና በነሐሴ ወር ውስጥ በኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ተፈርመው፣ ለኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተላኩ ተሽከርካሪዎችና ሌሎችም ዕቃዎች አስመጪዎች የባንክ ፈቃድ አጠቃቀም ችግሮችን በተመለከተ የተሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የተዘረዘሩባቸው ደብዳቤዎች፣ የኮሚሽኑን ውሳኔዎች ይዘረዝራሉ፡፡

በአስተዳደራዊ ውሳኔዎቹ ላይ ኮሚሽኑ የጠቀሳቸው የአስመጪዎች የባንክ ፈቃድ ሰነድ አጠቃቀም ችግሮች ተብለው በዋናነት የተዘረዘሩት ጉዳዮች ሁለት ናቸው።

በ2015 ዓ.ም. መስከረም 18 ቀን መጋቢት 14 እና ግንቦት 5 ቀን እንደ ተጻፉ የተገለጸባቸው ደብዳቤዎች ላይ ውሳኔዎቹ የተላለፉት፣ አንደኛ የተሽከርካሪም ሆነ ሌሎች ዕቃዎች አስመጪዎች ለኮሚሽኑ ባቀረቧቸው የባንክ ፈቃድ ሰነዶች፣ ፈቃዱ የተሰጠበትን ዕቃ በመተው የተፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ በመጠቀምና በፈቃዱ ላይ ያልተጠቀሰ የተለየ ተሽከርካሪ ወይም ዕቃ፣ ወይም ከተፈቀደላቸው መጠን በላይ ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ አስመጪዎችን በተመለከተ የተላለፉ ውሳኔዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።

በሁለተኛነት ውሳኔዎቹ ይመለከታቸዋል የተባሉት ደግሞ ለኮሚሽኑ ሐሰተኛ የባንክ ፈቃድ በማቅረብ ዕቃዎችን ወይም ተሽከርካሪዎችን አገር ውስጥ ያስገቡ አስመጪዎች ናቸው። 

ኮሚሽኑ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ያሳለፋቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች፣ በጥቅሉ የባንክ ፈቃድ አጠቃቀም ችግሮች ያሉባቸው ተብለው የተጠቀሱ አስመጪዎች ናቸው። 

የጉምሩክ ኮሚሽን በመስከረም ወር በወቅቱ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊ አቶ አብዲሳ ኢቲቻ ተፈርሞ በወጣ የውሳኔ ደብዳቤ ላይ ከተፈቀደ ቁጥር በላይ በመጨመሩ፣ ወይም በፈቃድ ሰነዶቹ ላይ ያልተጠቀሱ ዕቃዎችን አካተው ያስመጡ፣ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ ወደ አገር ውስጥ የገባ ዕቃ የተያዘባቸው፣ በፈቃዱ ላይ ከተገለጸው ሙሉ በሙሉ የተለየ ዕቃ ያስገቡ አስመጪዎች ለአንድ ጊዜ ብቻ ቀረጥና ታክስ ከፍለው ንብረታቸው ይሰጣቸው ይላል። 

ሕጋዊ የባንክ ፈቃዶች አለመሆናቸው በባንኮች ማረጋገጫ የቀረበባቸው ሐሰተኛ የባንክ ፈቃዶችን በመጠቀም ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ አስመጪዎችም እንዲሁ፣ ባስመጧቸው ዕቃዎች ላይ ሊከፈል የሚገባው ቀረጥና ታክስ ከፍለው፣ የቀረጥና ታክሱን መጠን አሥር በመቶ ቅጣት በመክፈል ዕቃቸው እንዲለቀቅላቸው ወስኗል።

በሌላ በኩል ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በወቅቱ የኮሚሽኑ የሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር ተወካይ ዘሪሁን አሰፋ ተፈርሞ የወጣው የውሳኔዎች ደብዳቤ፣ በሐሰተኛ የባንክ ፈቃድ ሰነድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ዕቃዎች እንዲወረሱ መወሰኑን ያሳያል። 

ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ተፈርሞ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተላከው የአስተዳደር ውሳኔ የትራንዚት ፈቃድ አግኝተው ወደ አገር ውስጥ ገብተው ትራንዚት በማጠናቀቅ የጉምሩክ ክሊራንስ ሥነ ሥርዓት የፈጸሙና በመፈጸም ሒደት ላይ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች አስመጪዎች ዝርዝር ሁኔታቸው በደብዳቤው ተብራርቶ ያልተገለጸ፣ ‹‹የባንክ ፈቃድ አጠቃቀም ችግሮች›› ያሉባቸው ተብሎ በጥቅሉ የተካተቱ አስመጪዎች መክፈል የሚገባቸውን ቀረጥና ታክስ መክፈላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የቀረጥና ታክሱን መጠን አሥር በመቶ ቅጣት ከፍለው እንዲስተናገዱ መወሰኑን ይገልጻል። 

በሐሰተኛ የባንክ ፈቃድ ወይም ማራዘሚያ ፈቃድ ወይም ደብዳቤ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ተሽከርካሪዎችና ዕቃዎች ጋር የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 1(መ) ላይ ማንኛውም ሰው አዋጁን ወይም በአዋጁ መሠረት የወጡ መመርያዎችን በማናቸውም ሌላ መንገድ የተላለፈ እንደሆነ ወንጀል የተሠራበት ሀብት የሚወረስ መሆኑን ይደነግጋል። እንዲሁም በሌሎች ሁለት አዋጆች፣ በአዋጅ ቁጥር 859/2006 እና በአዋጅ ቁጥር 1160/2012 መሠረት ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ውርስ እንዲደረጉ ይደነግጋል። 

የጉምሩክ ኮሚሽን ከመስከረም ወር ውሳኔዎቹ ጋር አያይዞ የሐሰተኛ ባንክ ፈቃድ ሰነድ ማቅረብ ሊያስከትለው የሚችለው የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተ በቀጣይ የሚመለከተው አካል እንዲታይ በቃለ ጉባዔው መወሰኑን ይገልጻል። ተያይዞም ግዴታቸውን በማይወጡ የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ በሠራተኞች መተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ በሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ስመጪዎችና የጉምሩክ አስተላላፊዎች ላይ በጉምሩክ አዋጅና ሌሎች አግባብነት ባላቸው የአገሪቱ ሕጎች መሠረት ተጠያቂ እንዲደረጉ ለሚመለከተው አካል መወሰኑንም ያትታል። 

በግንቦት ወር የውሳኔዎች ደብዳቤ ላይም ሐሰተኛ የባንክ ፈቃድ ሰነድ ለጉምሩክ በሚያቀርቡ አስመጪዎች፣ ተባባሪ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፣ እንዲሁም በሒደቱ ተሳታፊ የሆኑ የጉምሩክ አመራሮችና ሠራተኞች በሕግ እንዲጠየቁ ሰነዶቹ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ እንዲላኩና አፈጻጸሙ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት ያዛል። 

ከእነዚህ በተለየ በነሐሴ ወር በኮሚሽነሩ ተፈርሞ የባንክ አጠቃቀም ችግሮች ያሉባቸው ሰነዶች ባቀረቡ የተሽከርካሪ አስመጪዎች ላይ የተላለፈው አስተዳደራዊ ውሳኔ ደብዳቤ ላይ ግን፣ መሰል ዝርዝር መመርያዎች አልተላለፉም። 

በኮሚሽነር ደበሌ የተፈረመው ደብዳቤ፣ ‹‹በቀጣይ አስመጪዎች በተመሳሳይ ድርጊት ተሳትፈው ቢገኙ በሚፈጽሙት ጥፋት ላይ ለሚመጣ ተጠያቂነት ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ መሆኑን የጽሑፍ ማረጋገጫ ለሚስተናገዱበት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይስተናገዱ፤›› በሚል መመርያ ይደመድማል። 

እነዚህን ወጥነት የጎደላቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች በተመለከተ የኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አሰፋ ስለውሳኔዎቹ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አዎ የተለያዩ ውሳኔዎችን ስንሰጥ ነበር። አብዛኞቹ አስመጪዎች በሕግ መሠረት ነው የሚሠሩት፣ አንዳንድ ደግሞ ሕገወጥ ሥራዎችም የሚሠሩ ሊኖሩ ይችላሉ። በእነዚህ ላይ እንደ ማንኛውም ጊዜ ከበላይ አመራሮች ውሳኔዎች ይሰጣሉ። ይህም በዚያ ማዕቀፍ የሚታይ ነው። ከባንክ ፈቃድ አጠቃቀም ጋር ችግሮች ነበሩ። ችግሮቹን መሠረት አድርገን ነው ውሳኔዎች የሰጠነው፤›› ብለዋል። 

ኮሚሽኑን በመስከረም ውሳኔዎቹ ላይ የተጠቀሱ የባንክ ፈቃድ አጠቃቀም ችግሮች ያሉባቸው አስመጪዎች ለአንድ ጊዜ ብቻ ቀረጥና ታክስ ከፍለው እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸው የሚል ውሳኔ ያሳለፈበት ምክንያት ምንድነው የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹በዚህ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተሰጡ ውሳኔዎችን ማሳለፍ አስገዳጅ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ተሽከርካሪዎቹ አገር ውስጥ የገቡ በመሆናቸው ነው። አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ በደብዳቤው ከተላለፈው የተለየ ሌላ ውሳኔ መወሰን ከግብር ከፋዩም ሆነ ከመንግሥት አኳያ ሚዛናዊ አይሆንም በሚል ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም፣ ‹‹በወቅቱ በአስመጪዎች ዘንድ በተለያዩ ምክንያቶች የሚሰጧቸውን የባንክ ፈቃዶች በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታዎች ነበሩ። ስለዚህ ለኮሚሽኑ እነዚህ ላይ ምን ዓይነት ሚዛናዊ ውሳኔ ይሆናል ነበር ጥያቄው። ትክክለኛ የባንክ ፈቃድ እንዲያገኙ ያስቻላቸውን ዶላር ተጠቅመውበታል? ይወረስባቸው ቢባል የወሰዱትን ዶላር መመለስና የመሳሰሉ የተለያዩ ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ውሳኔዎች አሉ። እዚያ ውስጥ ከመግባት ይኼኛው ውሳኔ የተሻለ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ በመደረሱ ነው ውሳኔው የተሰጠው። ደብዳቤው ራሱም ራሱን ገላጭ (self-explanatory) ነው ብዬ ነው የማስበው፤›› በማለት አብራርተዋል። 

ሪፖርተር የግንቦትና የነሐሴ ወር አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ደብዳቤዎች ይዘት በመጥቀስ፣ ኮሚሽኑ የባንክ ፈቃድ ችግሮች ይህን ያህል ተደጋጋሚ ትኩረት የሚያሻቸው ሆነው ካገኛቸው፣ በየጊዜው የተለያዩ ውሳኔዎችን ከመስጠት ጉዳዩን የሚያስተናግድበት ወጥ የሆነ አሠራር ለምን ተግባራዊ አያደርግም? በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹በኮሚሽኑ የባንክ ፈቃድ ሰነዶች ችግሮችን ወጥ የሆነ ሁሉንም ማስተናገድ የሚቻልበት፣ ከሕግ ውጪ የሆኑትንም ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል፣ በአዋጅም፣ በመመርያም፣ በደንብም በማዕቀፍ ውስጥም እንዲታይ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያለው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ሪፖርተር ስለውሳኔዎቹ ያቀረባቸውን ሌሎች ጥያቄዎች በተመለከተ፣ ‹‹በኮሚሽኑ በኩል የተደራጀና የተሟላ ማብራሪያ እንዲሰጥ ካስፈለገ ሦስቱን ደብዳቤዎች አያይዛችሁ፣ ምን መረጃ እንደፈለጋችሁ ጠቅሳችሁ ብትልኩልን እኔ ለሚመለከተው የተቋሙ የበላይ አመራሮች በማቅረብ ምላሽ ይሰጥበታል፤›› የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ሪፖርተር በተጠየቀው መሠረት ደብዳቤዎቹን በማያያዝ የመረጃ ጥያቄ ደብዳቤ በማስገባት፣ የስልክ ጥሪዎችን፣ እንዲሁም አጭር የሞባይል ስልክ መልዕክቶችን ወደ ኃላፊው በመላክ ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ይህ ዜና ወደ ኅትመት እስከተላከበት ወቅት ድረስ አልተሳካም። 

የሐሰተኛ የባንክ ፈቃዶችን በተመለከተ ምን ያህል መሰል ሰነዶች በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል እንደሚመራላቸው ጥያቄ የቀረበላቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ፣ ‹‹ይህ የሚካተተው አስመስሎ በመሥራት የማጭበርበር ወንጀል (Forgery Crime) ውስጥ ነው። ለእዚህ ዘርፍ ደግሞ ከጉምሩክ ኮሚሽን በኩል የተመራ ተብሎ ተለይቶ በሪፖርት አይቀመጥም፤›› ብለዋል። 

የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሲያብራሩም፣ ‹‹ማንኛውም ዓይነት የሰነድ ማጭበርበር፣ የደብዳቤም፣ የፊርማም ይሁን የማኅተም የሚጣራው በፎረንሲክ የላቦራቶሪ ምርመራ ነው። ተለይቶ ከጉምሩክ የተመራ ተብሎ አይቀርብም። እንዲህ ዓይነት ምርመራዎች በፌዴራል ፖሊስ ምርመራዎች ነው የሚታዩት፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ የግድያ ወንጀል ሆኖ በውስጡ የሰነድ ማጭበርበር ሊያካትት ስለሚችል ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ በ2015 በጀት ዓመት የኮሚሽኑ ፎረንሲክ ምርመራ ክፍል 828 የተጭበረበሩ ናቸው የተባሉ ሰነዶችን እንዲያጣራ የቀረበለት ሲሆን፣ ከእዚህ ውስጥ በ821 ሰነዶች ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ውጤቱን ለሚመለከተው የምርመራ ክፍል እንደተመራ ያሳያል።