
ከ 7 ሰአት በፊት
በቦይንግ 737 ማክስ 9 ላይ በተደረገ ፍተሻ “ለተጨማሪ ማጠንከሪያነት” የሚያገለግሉ ልል ብሎኖች መገኘታቸውን ዩናይትድ አየር መንገድ ገለጸ።
ፍተሻው የተደረገው ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 9 በሩ በበረራ ወቅት ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ ነው።
የዩናይትድ አየር መንገድ ይህ አውሮፕላን ወደ አገልግሎት ከመመለሱ በፊት ከበር መሰኪያዎች ጋር የተያያዙ “የመግጠም ችግሮች ሊስተካከሉ” ይገባል ብሏል።
171 ተመሳሳይ አውሮፕላኖች በአሜሪካ ተቆጣጣሪ አካል ከበረራ ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ዩናይትድ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ “ቅዳሜ ዕለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍተሻ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ከበር መግጠም ጋር የሚዛመዱ ለምሳሌ ተጨማሪ ማጠንከሪያ የሚያስፈልጋቸው ብሎኖች አንዳሉ አግኝተናል” ብሏል።
የወደቀው በር መስኮት ያለው እና በአደጋ ጊዜ ለመውጫነት የሚያገለግል መሆኑ ታውቋል።
የአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን የአደጋ ጊዜ በር በአሜሪካዋ ኦሪጎን ግዛት በሚበርበት ወቅት ተገንጥሎ ወድቋል። በሩ በአንድ መምህር የአትክልት ስፍራ መገኘቱም ታውቋል።
አውሮፕላኑ በድንገተኛው አደጋ ምክንያት ያረፈ ሲሆን ከተሳፋሪዎቹም ሆነ ከአውሮፕላኑ አባላት አንድም ሰው ላይ ከባድ ጉዳት አልደረሰም።
በአሜሪካ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በዩናይትድ አየር መንገድ እና በአላስካ ባለቤትነት የሚተዳደሩ ናቸው። የቱርክ አየር መንገድ፣ የፓናማ ኮፓ አየር መንገድ እና ኤሮሜክሲኮም ተመሳሳይ ሞዴል ያላቸውን አውሮፕላኖች ለምርመራ ሲሉ ከሥራ ውጭ እንዲሆኑ አዘዋል።
ዩናይትድ ከሰኞ ጀምሮ 200 በረራዎችን መሰረዙን እና ማክሰኞ በተመሳሳይ ከፍተኛ የበረራ ስረዛዎች እንደሚኖሩ አስታውቋል።
“ሰኞ እና ማክሰኞ እያንዳንዳቸው ወደ 30 የሚጠጉ ስረዛዎችን በማስቀረት በሌሎች የአውሮፕላን አይነቶች አንዳንድ የታቀዱ በረራዎችን ማካሄድ ችለናል” ሲል ዩናይትድ አክሏል።
- ወታደራዊ ምሥጢር ለቻይና የሰጠው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኃላፊ በእስራት ተቀጣከ 7 ሰአት በፊት
- የሲንጋፖር ታዳጊዎች በሒሳብ ትምህርት ለምን ጎበዝ ሆኑ?ከ 8 ሰአት በፊት
- ወታደራዊ ምሥጢር ለቻይና የሰጠው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኃላፊ በእስራት ተቀጣከ 7 ሰአት በፊት
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ የአየር ጉዞን የሚቆጣጠረው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ባወጣው መግለጫ አየር መንገዶች በፍተሻ ወቅት ሊመለከቷቸው የሚገቡ የፍተሻ ዝርዝሮችን ማሳወቁን ገልጿል።
ኤፍኤኤ በመግለጫው አክሎ እንደገለጸው ሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ላይ “በግራ እና ቀኝ የሚገኙ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮችን፣ የበር ክፍሎችን እና ማያያዣዎችን በሙሉ መርምረው” እስኪያጠናቅቁ ድረስ ከበረራ ውጭ ሆነው እንደሚቆዩ አስታውቋል።
“አየር መንገዶች ማንኛውንም አውሮፕላን ወደ አገልግሎት ከመመለሳቸው በፊት በምርመራው በተገኘው ውጤት መሠረት የማስተካከያ እርምጃዎችን ማካሄድ አለባቸው” ሲል ገልጿል።
የአላስካ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 1282 አርብ አመሻሽ 16 ሺህ ጫማ (4.8 ኪሜ) ላይ እያለ በገጠመው ችግር ለማረፍ መውረድ መጀመሩን የበረራ መከታተያ መረጃዎች ያሳያሉ።
በበይነ መረብ የተጋሩ እና በኋላም በመርማሪዎች ይፋ የተደረጉ ምስሎች እንዳሳዩት ከሆነ የአውሮፕላኑ በር ተገንጥሎ ትልቅ ቀዳዳ ከመፈጠሩም በላይ የኦክስጅን ጭምብሎች ተንጠልትለዋል።
ተሳፋሪዎችን ጠቅሶ ዘ ኦሪጎኒያን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በሩ አካባቢ ተቀምጦ የነበረ የአንድ ወጣት ቲሸርት በተፈጠረው የግፊት ምክንያት አደጋ ምክንያት ተቀዳዷል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሚደረገውን ምርመራ የሚመራው የአሜሪከካው ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ (ኤንቲኤስቢ) እንዳስታወቀው አደጋው በደረሰበት የአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን ቀደም ብለው በተደረጉ ሦስት በረራዎች የግፊት ማስጠንቀቂያ መብራቶች እንደነበሩ አብራሪዎቹ ሪፖርት አድርገዋል።
አውሮፕላኑ “በፍጥነት ወደ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲመለስ” በማሰብ በውሃ ላይ ረዥም ርቀት በረራዎችን እንዳያደርግ መከልከሉን የኤንቲኤስቢ ኃላፊ ጄኒፈር ሆምዲ ተናግረዋል።
በተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች እና በተፈጠረው ጉዳይ መካከል ግንኙነት ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም ።
የአላስካ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ ደግሞ “ለመብረር ዝግጁ መሆኑን የሚገልጽ የፍተሻ መስፈርቶች መመሪያን ከኤፍኤኤ እና ከቦይንግ በምንጠብቅበት ወቅት የጥገና ቡድኖቻችን በአውሮፕላኑ የመሃል በር ላይ አስፈላጊውን ፍተሻ ለማድረግ የጥገና ባለሙያዎቻችን ዝግጁ ናቸው” ብሏል።
“የቦይንግ 737-9 ማክስ አውሮፕላኖችን ከበረራ ውጭ መሆናቸው ሥራችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እሑድ 170 የእሁድ በረራዎችን ሰኞ ደግሞ 60 በረራዎችን ስርዘናል። የበለጠ እንደሚሰረዝም ይጠበቃል” ብለዋል።
ቦይንግ ባወጣው መግለጫ “ደህንነት ቀዳሚ ትኩረታችን ነው። ይህ ክስተት በደንበኞቻችን እና በተሳፋሪዎቻቸው ላይ ላሳደረው ተጽዕኖ በጥልቅ እናዝናለን” ብሏል።
ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።
በአደጋዎቹ 346 ሰዎች ህይወት አልፏል። ሁለቱም አደጋዎች የተከሰቱት በበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሮች ስህተት ሲሆን አብራሪዎቹ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አውሮፕላኖቹ አንዲከሰከሱቡ አስገድዷቸዋል።