January 9, 2024 – DW Amharic 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀመሮ በርካታ በጎ ጅምሮች እንዳሉ የሚናገሩ እንዳሉ ሁሉ በበርካታ ጉዳዮች ብዙዎች የማይስማሙባቸው ነገሮች እንዳሉም ይነገራል። አናጋጋሪነታቸው ከቀጠሉ ጉዳዮች  ቅንጡ የሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። ከውጭና ከሃገር ውስጥ በተሰበሰበ የአገሪቱ ሀብት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት እየተገነቡ ያሉ የመናፈሻዎችና የቤተመንግስት ግንባታዎች፤ በቀጥታ ከመንግስት ካዝና በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ተደርጎ የሚካሄዱ የመንግስት መስሪያቤቶች እድሳት አሁንም አነጋጋሪነታቸው እንደቀጠለ ነው።

አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በተገባደደው የጎርጎሮሳውያኑ 2023 ዓ.ም በኢትዮጵያ በእርስበእርስ ጦርነቶችና ግጭት፤ እንዲሁም በድርቅ ምክንያት የምግብ እርዳታ የሚጠብቁ ወደ 23 ሚልዮን የሚጠጉ ወገኖች እንዳሉ ይናገራሉ።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ መደረሱን ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ። የንሮ ውድነቱ፤ የሰላም ሁኔታውና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በማንሳት እነዚህ ቅንጡ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው አደሉም በማለት ብዙዎች ይወቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይህን አይቀበሉም ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የተወካዮች ምክርቤት ስለበጀት ምንጩና አስተዳደሩ ሲጠይቃቸው ባላቸው የልመና ጸጋ ተጠቅመው ያመጡትን ገንዘብ ምክርቤቱ ሊቆጣጠራቸው እንደማችል ነበር  የገለጹት። እነዚህ አነጋጋሪ ፕጀክቶች አገሪቱ ካላት ኢኮኖሚያዊ ችግር አንጻር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው ወይ? በሚል ርእስ ላይ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችን አወያይተናል።

በነገራችን ላይ በዚህ ውይይት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሳተፉ ጋብዘን ነበር በዚህ ሳምንት እንደማይመቻቸው ስለተነገረን ማካተት አልቻልም።

ይህንን ተጭነው ያዳምጡት