ገብሪኤል አታል እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን
የምስሉ መግለጫ,ገብሪኤል አታል እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

9 ጥር 2024

ገብሪኤል አታል ቀጣዩ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተሾሙ።

ገብሪኤል አታል በ34 ዓመታቸው ጠቅላይ ሚንስትር መሆናቸው በፈረንሳይ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ትልቅ የመንግሥት ስልጣን የያዙ ፖለቲከኛ ያደርጋቸዋል።

በአሁኑ ወቅት የትምህርት ሚንስትር ሆነው እያገለገሉ ያሉት አታል፤ ለ20 ወራት በስልጣን ላይ የቆዩትን እና በፓርላማው ድጋፍ ያጡትን ኤሊዛቤት ቦርን ይተካሉ።

እአአ 2017 ላይ ማክሮን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነበር አታል የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆነው ወደፊት ብቅ ያሉት።

በምክር ቤት አባልነት ዘመናቸው አንደበተ ርዕቱ ሆነው መከራከራቸው የፕሬዝዳንቱን ቀልብ ስለመሳባቸው ብዙዎች ይስማማሉ።

ገና በ29 ዓመታቸው ሚንስትር መሆን ችለው ነበር። እአአ 2020 የመንግሥት ቃል አቀባይ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከዚያም የበጀት ሚንስትር በቅርቡ ደግሞ የትምህርት ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል።

አታል የትምህርት ሚንስትር ሳሉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሚለብሷቸውን አባያ ቀሚስ በትምህርት ቤት መከልከላቸው እና ሌሎች “ቆራጥ” የተባሉ እርምጃዎችን መውሰዳቸው የማክሮንን ይሁንታ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ይታመናል።

አባያ ከወገቡ ሰፋ ያለ ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ ሲሆን ወንድ ሙስሊሞች ከሚለብሱት ጀለቢያ ጋር የሚመሳሰል ነው።

በወቅቱ አታል “ወደ ክፍል ሲገባ የትኛው ተማሪ የትኛውን ሃይማኖት እንደሚከተል ማወቅ የለብንም” ብለው ነበር።

የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከማክሮን አስተዳደር ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያላቸው አታል ናቸው።