
9 ጥር 2024
ደቡብ ኮርያ ውሻን ማረድ እና ሥጋውን ለሽያጭ ማቅረብ በሕግ መከልከሉን የሚደነግግ ሕግ በፓርላማ አባላት ድጋፍ አውጥታለች።
ከሦስት ዓመት በኋላ ከ2027 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ሕግ፤ ለክፍለ ዘመናት የቆየውን የኮርያውያንን የውሻ ሥጋ የመብላት ልማድ ለማስቆም ያለመ ነው።
‘ቦሺንታንግ’ የተሰኘው ከውሻ ሥጋ የሚሰራው ወጥ በዕድሜ በገፉ ኮርያውያን ዘንድ የክት ምግብ ተደርጎ ይቆጠራል። ይሁን እንጂ በተመጋቢዎች ዘንድ ግን ያለው ተወዳጅነት እምብዛም እየሆነ የመጣ ሲሆን በወጣት የሀገሪቱ ዜጎች ዘንድም ተፈላጊ አይደለም።
በአዲሱ ሕግ መሠረት የውሻ ሥጋን መሸጥ እንጂ መመገብ በራሱ ሕገ ወጥ ድርጊት አይደለም። የውሻ ሥጋ ንግድ ላይ የሚያተኩረው ይህ ሕግ፤ ውሻን ሲያርዱ የተገኙ ሰዎች እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስር እንደሚቀጡ ደንግጓል።
ሥጋውን ለመሸጥ ሲሉ ውሻ ሲያረቡ እና ስጋውን ሲሸጡ የተያዙ ሰዎች ደግሞ እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እስር ይጠብቃቸዋል።
በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ የውሻ አርቢዎች እና የሬስቶራንት ባለቤቶች ይህንን ሥራ ለማቆም እንዲሁም አማራጭ ሥራ እና ገቢ ለመፈለግ ሦስት ዓመት ተሰጥቷቸዋል። ሕጉ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ይህ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።
- የ34 ዓመቱ ፖለቲከኛ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ9 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡት ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው ለምንድን ነው?9 ጥር 2024
- የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የጨዋታ ፕሮግራም9 ጥር 2024
የመንግሥት አሃዞች እንደሚያሳዩት በደቡብ ኮርያ ውስጥ 1,600 የውሻ ሥጋ የሚሸጥባቸው ሬስቶራንቶች እና 1,150 የውሻ አርቢዎች አሉ። እነዚህ አርቢዎች እና የሬስቶራንት ባለቤቶች ይህንን የንግድ ስራቸውን በምን አይነት መንገድ እንደሚያቆሙ የሚገልጽ እቅድ ለአካባቢዎቻቸው ባለስልጣናት እንዳቀረቡ ተገልጿል።
የደቡብ ኮርያ መንግሥትም በዚህ ሕግ ምክንያት የንግድ ስራቸው የሚቆም የውሻ አርቢዎችን፣ ሥጋ ሻጮችን እና የሬስቶራንት ባለቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመርዳት ቃል ገብቷል። ይሁንና መንግሥት ለነጋዴዎቹ ምን አይነት ካሳ እንደሚያቀርብ ገና አልተወሰነም።
ከ1980ዎቹ ጀምሮ የሀገሪቱ የቀድሞ መንግሥታት የውሻ ስጋን ለማገድ ቃል ሲገቡ የነበረ ቢሆንም ለውጥ ማምጣት አልተሳካላቸውም ነበር።
ለእንስሳት ባላቸው ፍቅር የሚታወቁት የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮን ሶክ የል እና ቀዳማዊት እመቤት ኪም ኪኦን ሂ፤ ስድስት ውሾች አሏቸው። ቀዳማዊት እመቤቲቷ የውሻ ሥጋ የመመገብ ልምድ እንዲቆም ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይህ እግድ እንዲተላለፍ በተመሳሳይ መልኩ ሲወተውቱ የነበሩ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች የሕጉን መውጣት ደግፈዋል። የውሻ አርቢዎች ግን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የውሻን ሥጋን የመብላት ልምዱ በወጣቶች ዘንድ እየቀነሰ መምጣቱን የሚያነሱት አርቢዎቹ ልምዱ በጊዜ ሂደት ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ መቆም ነበረበት ሲሉ ይከራከራሉ።
በተጨማሪም ብዙዎቹ የውሻ አርቢዎች እና የሬስቶራንት ባለቤቶች በእድሜ የገፉ መሆናቸውን በመጥቀስ በዚህ እድሜ ስራ መቀየር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ይናገራሉ።