
ከ 5 ሰአት በፊት
የናይጄሪያ መንግሥት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሕገ-ወጥ መንገድ አገር ውስጥ የገባ ነው ያለውን 11 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የዝሆን ጥርስ አቃጠለ።
የአገሪቱ የአካባቢ ሚንስትር ኢዚአቅ ሳላኮ የዝሆን ጥርስ እንዲቃጠል በተደረገበት ሥነ-ስርዓት ላይ በሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ በተሰማሩት ላይ ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደሌላ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን ብለዋል።
ምንም እንኳ የዝሆን ጥርስ ንግድ ከተከለከለ አስርት ዓመታት ቢያልፉም፤ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በመላው ዓለም በየዓመቱ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች ለጥርሳቸው ሲባል እንደሚገደሉ ይገልጻሉ።
ትናንት ማክሰኞ በናይጄሪያዋ መዲና አቡጃ እንዲቃጠል የተገደረው 2.5 ቶን ክብደት ያለው የዝሆን ጥርስ በአንድ ግዜ እንዲወድም ሲደረግ በናይጄሪያ ታሪክ ትልቁ ነው።
አንዳንዱ የዝሆን ጥርስ ተጠርቦ እና ወደ ጥበብ ሥራ ተቀይሮ ለገበያ የቀረበ ነበር።
ሚንስትሩ ሳላኮ የዝሆን ጥርሱ ተቃጥሎ ወደ ዱቄትነት ከተቀየረ በኋላ በዱቄቱ ዝሆኖች ያላቸውን ጥቅም እና ናይጄሪያ ዝሆኖችን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ሃውልት ይሰራበታል ብለዋል።
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡት ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው ለምንድን ነው?9 ጥር 2024
- የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የጨዋታ ፕሮግራም9 ጥር 2024
- አንዱ የሰውነት አካል ከሌላው አንጻር በፍጥነት እያረጀ መሆኑን ማወቅ ይቻላል?ከ 6 ሰአት በፊት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ናይጄሪያ ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ለሚደረጉ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ መተላለፊያ አገር ሆናለች። በናይጄሪያ በኩል የሚያልፈው የዝሆን ጥርስ ትልቁ የገበያ መዳረሻ ደግሞ እሲያ አህጉር መሆኑን የዱር እንስሳት መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።
ባለፈው ጥቅምት ወር በናይጄሪያ 4 ቶን የሚመዝን ፓንጎሊን የተባለች እንስሳት ቅርፊት በተመሳሳይ መልኩ እንዲወድም ተደርጎ ነበር።
አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ እአአ 1970ዎቹ በአፍሪካ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዝሆኖች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ የዝሆን ቁጥር ከ500ሺህ ያነሰ ነው። በናይጄሪያ ደግሞ ያሉት የዝሆኖች ቁጥር ከ400 እንደማይዘል ይገመታል።
ዝሆኖች ለጥርሳቸው ብቻ ሳይሆን ሰብል ሲያወድሙ ወይም ወደ ሰዎች መኖሪያ አካካቢ ሲጠጉ ይገደላሉ።