የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የፕሮስቴት ካንሰር ታማሚ መሆናቸው ተገለጸ።

ከ 4 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የፕሮስቴት ካንሰር ታማሚ መሆናቸው ተገለጸ።

በታህሳስ ወር የፕሮስቴት ካንሰርን ለማከም በተደረገ ቀዶ ህክምና ውስብስብ ችግር እንዳጋጠማቸው የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ህክምናውን ተከትሎ የተፈጠረው ኢንፌክሽን ኦስቲን በድጋሚ ሆስፒታል ደርሰው ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል እንዲገቡ አድርጓቸው ነበር።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለፕሮስቴት ካንሰር ህክምናው ያወቁት ማክሰኞ ዕለት ነው ሲል ዋይት ሃውስ ተናግሯል።

ስለሦስት ቀናት የሆስፒታል ክትትላቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዳልሰሙ ከታወቀ በኋላ የ70 ዓመቱ ኦስቲን ከፍተኛ ትችት ገጥሟቸዋል።

በኋላም “ህዝቡ በአግባቡ እንዲያውቅ” ባለማድረጋቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

የመከላከያ ሚንስትሩ የአሜሪካ ጦር የእዝ ሰንሰለት በተመለከተ ከፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ ይቀመጣሉ። በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የፕሬዚዳንቱ ካቢኔ አባላትም አንዱ ናቸው። መረጃውን ለዋይት ሃውስ ሳያሳውቁ መዘግየታቸው በባይደን አስተዳደር የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን እና የግልጽነት ጉዳዮችን ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

ፕሮስቴት ካንሰር ፕሮስቴት ዕጢ ላይ የሚከሰት እና ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ጥቁር ወንዶችን የበለጠ ያጠቃል።

ኦስቲን ትናንት ማክሰኞም በሆስፒታል ማሳለፋቸውን ፔንታገን አረጋግጧል። ቃል አቀባዩ መቼ ከሆስፒታል እንደሚወጡ መረጃ አልሰጠም።

ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ኦስቲን በጥሩ ሁኔታ ማገገማቸውን ቀጥለዋል። በጥሩ መንፈስ ከከፍተኛ ባልደረቦቻቸው ጋር እንደተገናኙ እና የዕለት ተዕለት ተግባሩን በዓለም ዙሪያ መከታተላቸውን ይቀጥላሉ” ብለዋል።

ማክሰኞ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኦስቲን ህክምና ሁኔታ ዋይት ሃውስ የያዘበትን መንገድ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ባይደን የፕሮስቴት ካንሰር ምርመራውን በተመለከተ “ትናንት” ተነግሯቸዋል።

“ኦስቲን የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለባቸው እስከትናንት ድረስ ዋይት ሃውስ ውስጥ ማንም አያውቅም ነበር” ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ ምላሽ ለሚንስትሩ ጤና መጨነቅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ኪርቢ መረጃ ልውውጡ ክፍተት እንዳለበት ግን አምነዋል።

ኪርቢ “በዚህ መንገድ መሄድ አልነበረበትም” ብለዋል።

ኦስቲን የሆስፒታል ቆይታቸውን በተመለከተ ለዋይት ሃውስ እና ለከፍተኛ የፔንታጎን ባለስልጣናት ማሳወቅ አለመቻላቸው ውዝግብ አስነስቷል። የኦስቲን ምክትል የሆኑት ካትሊን ሂክስ አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንዲወስዱ ቢጠየቁም ስለሆስፒታል ቆይታቸው ግን አልተነገራቸውም ነበር።