ነፍሰ ጡር
የምስሉ መግለጫ,መጸነስ የሚፈልጉ ሴቶችን የሚተባበሩ ወንዶች ”ይፈለጋሉ” የሚለው ማጭበርበሪያ

ከ 3 ሰአት በፊት

ብዙ ሺዎቹ እንዴት እንደተጭበረበሩ ለመናገር ያፍራሉ።

መንገሽ ኩማር ግን ስሜ ከተቀየረ ችግር የለውም አለ።

አዲሱ የበይነ መረብ ሥርቆት የሚያማልል ነው።

በሕንድ ሃብታም ሴቶች አሉ። ነገር ግን ማርገዝ አልቻሉም። የሚያስረግዛቸው ወንድ ይፈልጋሉ። ጽንሱ ከሰመረ ያ ሰው ግማሽ ሚሊዮን ሩፒ ይከፈለዋል የሚል “አዲስ የሥራ ዕድል” ይተዋወቃል።

ይህ በርካታ ድሃ የሆኑ ሕንዳውያን ወንዶችን ሳያማልል አልቀረም።

ኩማር የተባለው ሕንዳዊ ጎልማሳ ታሪኩን እንዲህ ይናገራል።

“ሰሜናዊ ሕንድ ቢሃር የምትባል ግዛት ነው የምኖረው። የሆነ ቀን አንድ ቪዲዮ አየሁ። ተጫንኩት” ይላል። ቪዲዮን ተመልክቶ አድራሻውን ካስቀመጠ በኋላ፤ “በ10 ደቂቃ ስልኬ ጠራ። ማን ነህ አልኩ። ስሜ ሳንዲፕ ሰር ይባላል። ለአንድ ሙምባይ ለሚገኝ ኩባንያ ነው የምሠራው። እና አንዲት ሴት አለች። ካስረገዝካት ግማሽ ሚሊዮን ሩፒ ትከፍላለች አለኝ። መመዝገቢያ 799 ሩፒ ያስከፍላል ብሎ አስረዳኝ።” ይላል።

“ግማሽ ሚሊዯን ሩፒ የሦስት ዓመት ደመወዜ ነው። ለምን ዕድሌን አልሞክርም አልኩኝ። ነገር ግን ይህ ገንዘብ የሚከፈልህ ጽንስ ከጸነሰች ብቻ ነው አለኝ።

ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ብሆንም ገንዘቡ አጓጓኝ። በዚያ ላይ ድሃ ነኝ። ከዚያ በኋላ በነበሩ ሁለት ሳምንታት ደጋግሞ ደወለ።

የተለያዩ ሰነዶችን ይልካል። ሰነዶቹ ላይ መፈረም አለብህ ይለኛል። 2550 ሩፒ የፍርድ ቤት ማስረጃ ለማውጣት፣ 4500 ሩፒ መጠባበቂያ ክፍያ፣ 7998 ደግሞ ለሚከፈለው ግማሽ ሚሊዯን የግብር ደረሰኝ ክፍያ እንድከፍል ነገረኝ።

ለክፍያዎቹ ደረሰኞችና የፍርድ ቤት ወረቀቶችን ይልክልኛል። ሰነዶቹ ላይ ስሙ፣ ፊርማውና የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ፎቶ አለ።

ዋናው ሰነድ “የልጅ ልደት ሰርተፍኬት ስምምነት” የሚል ሲሆን ከስር “የጽንስ ማረጋገጫ ሰነድ” የሚል አለበት። ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳል።

ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ሰርተፍኬት ከሥሩ የአሜሪካዊቷ የቴሌቪዥን አሰናጅ ኦፕራህ ዊንፍሬህ ፊርማን የመሰለ ደማቅ ፊርማ እንዳለበት አስተውሏል።

ኩማር ታሪኩን ይቀጥላል።

“ከዚያ ቀጥሎ በነበሩ ቀናት የስምንት ሴቶችን ፎቶ ላከልኝ። ከነዚህ መካከል ማስረገዝ የምትፈልገው የትኛዋን ነው ብሎ ጠየቀኝ። የመረጥኳት ሴት እኔ ያለሁበት ከተማ መጥታ ሆቴል ከያዘች በኋላ እንደምትደውልልኝ ተነገረኝ።”

ቃል የተገባልኝ ገንዘብ መቼ ነው የሚለቀቅልኝ ብዬ ስጠይቅ ደረሰኝ ተላከልኝ። ደረሰኙ ላይ 512ሺህ 400 ሩፒ ተጽፎበታል። ነገር ግን ገንዘቡ አልተለቀቀም። የሚለቀቀው የገቢ ግብር ስከፍል ብቻ እንደሆነ ተነገረኝ።

የገቢ ግብር ስንት ነው አልኩ?

12ሺህ 600 እንደሆነ ተነገረኝ።

በጣም ተበሳጨሁ። ገንዘብ የለኝም። የወር ገቢዬን ለናንተ ከፍያለሁ ብዬ ነገርኩት።

ሳንዲፕ ሰር ግን ግማሽ ሚሊዮኑ ክፍያ ሊፈጽምልኝ እንደማይችል እርግጡን ነገረኝ። የገቢ ግብር መክፈል ካልቻልኩ ችግር ውስጥ እንደምገባ አስፈራራኝ።

ተይዞ ያለ ግማሽ ሚሊዮን ሩፒ ባንኬ ላይ እንደሚታይ እና ፖሊስ በቁጥጥር ሥራ እንደሚያውለኝ ነገረኝ። ገቢ በመሰወር ልከሰስ እችላለሁ ብዬ ፈራሁ።

በጣም ደንግጬ 10 ቀናት ስልክ አጥፍቼ ቤት ተደበቅኩ።

ኩማር ለቢቢሲ እንደተናገረው በዚህ ሁሉ ወቅት እየተጭበረበረ ሊሆን እንደሚቸል አልጠረጠረም። ምክንያቱም ግለሰቡ የራሱን መታወቂያ ልኮለታል። የሕንድ ፖሊስ አባል እንደሆነ ገልጾለታል። በዋትስአፕ ምስሉ ላይ ደግሞ ልጅ ያቀፈች ሴት ምስል ነው ያለው። እነዚህ ተደማምረው አሳመኑት።

የሳይበር ባለሙያው ፓቫን ዱጋል እንደሚለው በሕንድ ብዙ ሰው ሌላውን የማመን ችግር አለበት። ተጠራጣሪ አለመሆኑ ደግሞ ዋጋ እያስከፈለ ነው።

ይሁንና ይህ ‘የሚያስረግዝ ወንድ አዲስ የሥራ ዕድል’ የሚለው ማጭበርበር ጥንቃቄ የተሞላበትና ማንንም ወንድ የሚያማልል መሆኑን ዱጋል አይክድም።

“አዲስ ፈጠራ ይዘው ነው የመጡት” ይላል።

“ከሴት ጋር ስለተኛህ ግማሽ ሚሊዯን ታገኛለህ ስትባል እንዴት እምቢ ትላለህ?”

ኩማር አጭበርባሪው ሰው አሁንም እየደወለለት ነው።

“መቼ ለታ ደውሎ ማርገዝ የምትፈልገው ማዳም ወደ ኩባንያችን እየደለች ነው። በየቀኑ ነው የምትደውለው” አለኝ። 3000 ሩፒ የገቢ ግብር ከከፈልኩ 90ሺህ ሩፒ ወደ አካውንቴ እንደሚገባ ነገረኝ።”

ኩማር በተራው አሁን ለሳንዲፕ ሰር ደጋግሞ እየደወለ ነው። ስልኩን ግን አያነሳለትም።

“ምን እንደማደርግ አላውቅም። የወር ደመወዜን ተበላሁ። ለቤተሰቤ የምልከው ገንዘብ የለኝም። ባለቤቴ በጣም ተበሳጭታ ዘግታኛለች። አጭበርባሪዎቹን መንግሥት የገቡበት ገብቶ ይዞ ከፍተኛ ቅጣት ይቅጣልኝ፤ ሌላ ምን እላለሁ” ብሏል።